Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
16ቱ አለም አቀፍ የፀረ ፆታዊ ጥቃት ቀናት የንቅናቄ እቅድ በጋራ ለመተግበር እና ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆናቸውን የልማት አጋራት ገለፁ
የዘንድሮው አለም አቀፍ የፀረ ፆታዊ ጥቃት ቀናት የንቅናቄ መርሐግብርን አስመልክቶ የተዘጋጀውን ሀገራዊ እቅድ ለባለድርሻ አካላት ለማስተዋወቅና በጋራ ለመተግበር ያለመ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በውይይቱም የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ክስተቶች ምክንያት ሴቶችንና ታዳጊዎች ለጥቃት የሚጋለጡበትና ውስብስብ ለሆኑ ችግሮች የሚዳረጉበት ሁኔታ መኖሩን ገልፀዋል። በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀም ጥቃትን ለመከላከልና ለተጎጂዎች ምላሽ ለመስጠት መንግስት በኩል የሚያስችሉ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን በሰፊው አብራርተዋል። በተለያዩ አካላት እየተደረገ ላለው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል። ከጥቃት ነፃ የሆነ ትውልድና ጥቃትን የማይታገስ ማህበረሰብ ለመገንባት የሚደረገው ጥረት ዘላቂና ውጤታማ እንዲሆን በቅንጅት መረባረብ ያስፈልጋል ብለዋል።

የዘንድሮውን አለም አቀፍ የፀረ ፆታዊ ጥቃት ቀን ከአዳራሽ ውጭ ማህበረሰቡ ግንዛቤ በማስጨበጥ፣ የጥቃት ተጎጂዎችንና አገልግሎት ሰጪ ማዕከላትን መደገፍና ማጠናከር በሚያስችሉ እና ተጨባጭ ውጤት በሚያመጡ ተግባራት ለማክበር የንቅናቄ መርሐግብር መዘጋጀቱን ጠቁመዋል። ለሀገራዊ እቅዱ ስኬታማነትም ባለድርሻና አጋር አካላት ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ክብርት ሚኒስትሯ ጠይቀዋል። በውይይቱ የተገኙ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሃላፊዎችና ተወካዮች በበኩላቸው፥ 16ቱ አለም አቀፍ የፀረ ፆታዊ ጥቃት ቀናት የንቅናቄ እቅዱን በጋራ ለመተግበር እና ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
