የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ህፃናትና ታዳጊዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ተገለፀ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ከላይት ፎር ዘ ወርልድ አለም አቀፍ ስራ አስፈፃሚ ከሆኑት ማሆን ሊዘር እና ልዑካን ቡድናቸው ጋር በአካል ጉዳተኞች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ዙሪያ ተወያይተዋል።

በውይይቱ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደጠቀሱት ድርጅቱ አካል ጉዳተኞችን ለመደገፍ ከሚያከናውናቸው ተግባራት ጎን ለጎን የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል። በተለይም የአእምሮ እድገት ውስንነት ያላቸውን ህፃናት በትምህርት፣ በጤናና በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው ብሎም ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት ላይ ትኩረት በማድረግ እንዲሰራ አሳስበዋል።

በተጨማሪም ድርጅቱ በኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞችን ለማካተት ለመደገፍ የሚሠራውን ስራ አድንቀው የአገልግሎት ተደራሽነቱን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች አጠናክሮ እንደቀጥል ጠይቀዋል። የላይት ፎር ዘ ወርልድ አለም አቀፍ ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ማሆን ሊዘር በበኩላቸው ድርጅቱ በኢትዮጵያ የሚያከናውነውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀው ከሚኒስቴር መ/ቤቱ ጋርም ስትራቴጂክ አጋር በመሆን እንደሚሰራ ቃል ገብተዋል።

Please follow and like us: