Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ለአረጋውያን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆን ሄልፕኤጅ ኢንተርናሽናል ድጋፉን እንዲያጠናክር ክብርት ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ጥሪ አቀረቡ
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ የሄልፕኤጅ ኢንተርናሽናል ዋና ስራ አስፈፃሚ ሚስተር ቼራን ማቲውስ እና ልዑካን ቡድናቸውን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በውይይታቸውም፥ የማህበራዊ ጉዳይ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ አረጋውያን በእድሜ መግፋት፣ በጤና እክል እንዲሁም በተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ተጎጂ መሆናቸውን አንስተው ሚኒስቴሩ የአረጋውያንን መብትና ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል። የአረጋውያን መብቶችና ፍላጎቶች ትኩረት እንዲሰጠውና ማህበራትን ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራትን ከሄሌፕኤጅ ኢትዮጵያ ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን በመግለፅ ምስጋና አቅርበዋል።
አረጋውያንን የተመለከቱ ደጋፊ የህግ ማዕቀፎች እንዲኖሩ፣ በግንዛቤ ፈጠራና በአቅም ግንባታ እንዲሁም በስርዓት ዝርጋትና የተጀመሩ ተግባራትን ማስቀጠል በሚያስችሉ የትብብር መስኮች ዙሪያ አጋርነት የበለጠ ማጠናከርና በጋራ መስራት እንደሚያፈልግ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ የአረጋውያንን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ስትራቴጂክ ጉዳዮች ዙሪያ ከሄልፕኤጅ ኢንተርናሽናል ጋራ በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኗን ገልፀው በዘርፉ የሚከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ ድጋፉን እንዲያጠናክር ክብርት ሁሪያ አሊ ጥሪ አቅርበዋል።የሄልፕኤጅ ኢንተርናሽናል ዋና ስራ አስፈፃሚ ሚስተር ቼራን ማቲውስ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ አለም አቀፍ የአረጋውያን ኮንቬንሽንና የአረጋውያን ፖሊሲ ቀረፃ ላይ ንቁ ተሳትፎ እንድታደርግና ገንቢ ሚናዋን እንድትጫወት ጠይቀዋል። በቀጣይም ቅድሚያ በሚሰጣቸው የትብብር መስኮች ዙሪያ የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ለተፈፃሚነቱ የስራ ሃላፊዎቹ በጋራ ለመስራት ከስምምነት ደርሰዋል።
