ታዊ ጥቃትን በመከላከልና በማስቆም ረገድ ወንዶች አጋርነታቸውን እንዲያሳዩና የመፍትሔ አካል እንዲሆኑ ተጠየቀ

ጾታዊ ጥቃትን በመከላከልና በማስቆም ረገድ ወንዶች አጋርነታቸውን እንዲያሳዩና የመፍትሔ አካል እንዲሆኑ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሙና አህመድ ጥሪ አቀረቡ።

‎ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ እንዳሉት፥ ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃትና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በሴቶችና ህጻናት ላይ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እያስከተሉ ይገኛሉ። ‎ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላም በተጎጂዎች አእምሮና ስነልቦና ላይ ጥሎት የሚያልፈው ጠበሳ በቀላሉ የሚሽር ባለመሆኑ አስቀድሞ ለመከላከል ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን ተጎጂዎች ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንዲያገኙ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል። ጾታዊ ጥቃት ከግለሰብ ጀምሮ በማህበረሰብና በሀገር ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ከግምት ውስጥ በማስገባት መንግስት ጠንካራ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ ‎ለአብነት ለሴቶችና ህጻናት ሰብዓዊ መብት መከበር ጉልህ አስተዋጽኦ ያላቸው አለም አቀፍ ስምምነቶችን ተቀብሎ ከማጽደቅ ባሻገር አላሰራ ያሉ ህጎችን ለማሻሻል፣ አዳዲስ የአሰራርና የአደረጃጀት ለውጦችን ለማካሄድ፣ የተቋማትን አቅም ለማጠናከርና የተቀረጹ የህግ ማዕቀፎችን በስራ ላይ እንዲውሉ መደረጉን በማሳያነት አንስተዋል።

‎ጥቃትን ለመከላከልና ለማስቆም በተደረገ የጋራ ጥረትም በርካታ ውጤታማ ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም አሁንም ድርጊቱ እየተፈጸመ ያለበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመዋል። በመሆኑም ጥቃትን የማይታገስና አስቀድሞ መከላከል የሚችል ማህበረሰብ ለመፍጠር የተጀመረው ርብርብ የበለጠ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡ ‎ድርጊቱን በመከላከልና በማስቆም ረገድ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በተለይም ደግሞ ወንዶች አጋርነታቸውን እንዲያሳዩና የመፍትሔ አካል እንዲሆኑ ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ ጥሪ አቅርበዋል።

Please follow and like us: