Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የአቋም መግለጫ
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጾታዊ ጥቃት እያደረሰ ያለውን ግለሰባዊ፣ ማሕበረሰባዊ ብሎም ሀገር አቀፋዊ ጉዳት በመረዳት ያወጡት የአቋም መግለጫ
***
ቅዱሳት የሃይማኖት መጻህፍት ጾታዊ ጥቃትን የሚቃወሙ በመሆኑ እና ፈጣሪ ሴቶችን እንድንወድ እንጂ ጥቃት እንድንፈጽምባቸው ስላላዘዘን የጾታ ጥቃትን በጽኑ እናወግዛለን።
እኛ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ጾታዊ ጥቃትና እንዳይፈፀም ከምንሰጠው ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ጐን የሃይማኖት አባቶች የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ ስለሆነ በሁሉም የእምነት ተቋማቶቻችን ድርጊቱን ለማስቆም የሚደረገውን ዘመቻ አጠናክረን ለመቀጠል ተስማምተናል፡፡
የጾታ ጥቃትም ሆነ የጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መንስኤያቸው የመንፈሳዊ ሕይወት ውድቀት ወይም የስብዕና መንጠፍ በመሆኑ ለተከታዮቻችን በቋሚነት እና በተከታታይነት የሥነ-ምግባር ትምህርት ለመስጠት ቃል እንገባለን፡፡
በጾታዊ ጥቃት መከላከል ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመቀራረብ በጋራ ለመስራት ተስማምተናል፡፡
የጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ወገኖቻችንን ባለን አቅም ሁሉ ለመደገፍና ለማቋቋም እንዲሁም ለተጠቂዎች ተገቢውን ፍትሕ እንዲያገኙ ከሕግ ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመስራት ተሰማምተናል፡፡
ሴቶች ከጥቃት እንዲጠበቁ የወንዶች አጋርነትና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ስለምናምን ወንዶች ድርጊቱን እንዲቃወሙና በቸልታ እንዳያልፉት ለማስተማር ተስማምተናል፡፡
በቤተሰብ አባላት መካከል እንዲሁም በማህበረሰቡ ወስጥ ጥቃት እንዲቆም እና ጠንካራ ፍቅር የሞላበት ቤተሰብ እና የሰላም፣ የፍቅርና የፍትህ ማህበረሰብ ለመገንባት በጸሎት፣ ውይይትና በተግባር ለመትጋት ተስማምተናል።
ማንኛውንም በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃትን ለማስቀረት የሁሉም ቤተ-እምነት ተቋማት የማስተባበር እና በጋራ የመስራት ጥረታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ዝርዝር ኃላፊነቶችን ከግብ ለማድረስ ቃል የገባን ቢሆንም በመንግሥት በኩል ደግሞ ትውልዱን ከጥቃትና ከጥፋት ለማዳን፡-
* ልቅ ጾታዊ ግንኙነት የሚገፋፋ የሚዲያ ማስታወቂያዎች እና ፕሮግራሞች ማስተካከያ እንዲደረግባቸው፤
*ትውልዱን በተለይም ወጣቱን ወደ ከፍተኛ ውድቀት የሚያመሩ የምሽት ዳንስ ቤቶች፣የሀሺሽ ቤቶች፣ የጫትና የአደንዛዥ እፅ መጠቀሚያ ቤቶችና ልቅ የወሲብ ፊልሞችን የሚያሳዩ ፊልም ቤቶች በአፋጣኝ ህጋዊ እርምጃ በቋሚነት እንዲወሰድባቸው፣ *ምእመኖቻችንን በተለይም ወጣቱን ትውልድ ለጥፋት የሚዳርጉ የህትመት ውጤቶችን መንግሥት ካለበት ኃላፊነት አንፃር ክትትል በማድረግ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ በድጋሚ አብክረን እናሳስባለን፡፡
