Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የቅድመ ልጅነት ፕሮግራሞች መስፋፋት የሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የጎላ ፉይዳ እንደሚኖረው ተገለፀ
ይህ የተገለፀው በህፃናት የቅድመ ልጅነት ፕሮግራምና በሴቶች የኢኮኖሚያዊ ማጎልበት ዙሪያ የሚመክር ሀገር አቀፍ ውይይት በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አስተባባሪነት በባለ ድርሻ አካለት ጋር ትብብር በተካሄደበት ወቅት ነው ።

በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችና ህፃናት ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ ክብርት ሂክማ ከይረዲን ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለፁት መንግስት የሴቶችን ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ለማረጋገጥ እንዲሁም የህጻናትን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ ያሉበትን አለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና ህገ መንግስታዊ ኃላፊነቶቸ ለመወጣት ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል። የቅድመ ልጅነት ፕሮግራሞች መስፋፋት የሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የጎላ ፉይዳ እንደሚኖረው ጠቅሰው በተለይም ሴቶች በገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ በሙሉ አቅማቸውና በብቃት ተሳታፊ እንዲሆኑ ፣ ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ እና በራሳቸው የገንዘብ ነፃነት እንዲኖራቸው ያግዛል ብለዋል። ይህም የሴቶችን ተሳትፎ በመጨመር የሀገሪቱን ምርታማነት ከፍ በማድረግ እና ድህነትን በመቀነስ ለዘላቂ ልማት ስኬት ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ጠቅሰዋል።

ህፃናት በመልካም አስተዳደግና ስብዕና ለመቅረጽ፣ ለተሟላ እድገታቸው አስፈላጊ የሆኑ አገልግሎቶችን ለማሟላት፣ መብትና ደህንነታቸውን የሚያስጠብቁ አደረጃጀቶች፣ የህግና የፖሊሲ ማእቀፎች፣ አሰራር ሥርዓቶችን የማውጣት፣ የመዘርጋትና የመተግበር እንዲሁም በህፃናት ድጋፍና እንክብካቤ ዙሪያ የሚሰሩ አካላትን የመደገፍና የማበረታታት ስራዎች በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ከትምህርት ሚኒስቴር እና ከጤና ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን በስራ ላይ ያለውን ብሔራዊ የቅድመ ልጅነት ዘመን እድገትና ትምህርት ፖሊሲ ማዕቀፍ ወደ ተጨባጭ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለመግባት የሚያስችል የማስፈፀሚያ ስትራቴጂ በማዘጋጀት፣ የተለያዩ ስልጠናዎችና የልምድ ልውውጦችን ለክልሎች በማዘጋጀት ተግባሩ እንዲስፋፋና እንዲጠናከር አየሠራ እንደሚገኝ ገልፀዋል ። በውይይቱ የፌደራልና የክልል የሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት ስትራቴጂያዊ ፕሮግራም አስተዳደር ቢሮ (SPMO) ፣ አፍሪካ የቀዳማይ ልጅነት ልህቀት ማዕከል ፣ የከተማና መሰረተ ልማት ሴክተር፣ አጋር የልማት ድርጅቶች (SNV and Mercy Corps) እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
