Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ከጥቃት ነፃ የሆነ ትውልድና ጥቃትን የማይታገስ ማህበረሰብ ለመገንባት የሚደረገው ጥረት ዘላቂና ውጤታማ እንዲሆን በቅንጅት መረባረብ ያስፈልጋል – ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ
የዘንድሮው አለም አቀፍ የፀረ ፆታዊ ጥቃት ቀን እና አለም አቀፉ የህፃናት ቀን በጋራ በኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የመከላከያ ጤና ዋና መምሪያ በተለያዩ ዝግቶች በጋራ ተከብሯል።
በመርሐግብሩ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደገለፁት፥ በማንኛውም ሁኔታ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈጸሙ አካላዊ፣ አእምሯዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ወሲባዊ ጥቃቶች የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሀገራችን ፈርማ የተቀበለችውን ስምምነት የሚፃረር ተግባር በመሆኑ ድርጊቱን ማውገዝና አምርረን መታገል ይኖርብናል ብለዋል። ድርጊቱ ተደራራቢና የተራዘመ ጉዳት ያስከትላል ያሉት ክብርት ሚኒስትሯ ከጥቃት ነፃ የሆነ ትውልድና ጥቃትን የማይታገስ ማህበረሰብ ለመገንባት የሚደረገው ጥረት ዘላቂና ውጤታማ እንዲሆን በቅንጅት መረባረብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ጀግናው ሠራዊት እየተዋደቀ የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ትልቅ መስዋዕትነት እየከፈለ፤ ጥቃትን አስቀድሞ ለመከላከልና ለማስቆም የሚያስችል አሰራር ዘርግቶ እየተገበረ በመሆኑ እንኮራበታለን ሲሉ ገልፀዋል።
ሚኒስቴሩ ጥቃትን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ተግባራትን በቅንጅት እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ ጤና ምመሪያ ለሚሰራቸው ስራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።የመከላከያ ጤና ዋና መምሪያ ምክትል እና የጦር ሃይሎች ኮምፐርሄንሲቭ ስፔሼላይዝድ ሆስፒታል አዛዥ ክቡር ሜጀር ጀነራል ዶ/ር ሀይሉ እንዳሻው በበኩላቸው፥ አለም አቀፍ ሁነቱ ከመታሰቢያነት ባለፈ እንደሰው – እንደወታደርና እንደጤና ባለሙያ ሴቶችና ህፃናትን ከጥቃት ለመከላከል፣ በየትኛውም ተግባር ውስጥ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ለማስቻልና ለመደገፍ ቃል የምንገባበትና የምንተገብርበት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በዕለቱ ሚኒስቴሩ ለመከላከያ ጤና ዋና መምሪያ የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን በስጦታ አበርክቷል።
