ከአውሮፓ ህብረት እና ከስፓኒሽ የልማት ድርጅት እንዲሁም ከዩ ኤን ውመን እና ከተ.መ.ድ የስነ ህዝብ ድርጅት በተገኘ የ6.8ሚ ዩሮ (1.1 ቢ ብር በላይ) ድጋፍ የሚተገበር ‎የስርዓተ ፆታ እኩልነትን ለማስፈን እንዲሁም ተቋማዊ አቅምን በማጠናከር በየደረጃው የሚገኙ ተቋማዊ መዋቅሮችን ውጤታማ ማድረግ የሚያስችል ፕሮግራም ይፋ ሆነ::

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ የስርዓተ ፆታ ድርጅቶችን ተቋማዊ አቅምን ለማጠናከርና ውጤታማ ለማድረግ (Strengthening the Institutional Capacity of the National Gender Machinery in Ethiopia) የሚያስችል ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት የሚተገበር ፕሮግራም በዛሬው ዕለት ይፋ አድርገዋል።

‎በ‎ፕሮግራሙ ማስጀመሪያ መርሐግብር የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ፥ ኢትዮጵያ የስርዓተ ፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አበረታች እርምጃዎችን እየወሰደች ትገኛለች ብለዋል። ‎ክብርት ሚኒስትሯ የአካቶ ትግበራን መሬት ለማስነካት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአሰራር ስርዓት ዘርግቶና ተገቢውን የክትትል፣ ድጋፍና ተጠያቂነትን የማስፈን ስራን ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ በመሆኑ በተለያዩ ተቋማት ለውጦች እየታዩ እና መነቃቃቶችና ምላሽ ሰጪነት እየተፈጠሩ መምጣቱን ጠቁመዋል። ‎እንደሀገር ሴቶችን፣ ስርዓተ ጾታንና ሌሎች ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎችን የሚመለከቱ ፓሊሲዎችና ስትራቴጂዎች የተቀረፁ ቢሆንም ጉዳዩን መሬት ለማስነካትና ቀጣይነት ያለውን ለውጥ እያረጋገጡ ለመሄድ ግን የሰለጠነ የሰው ሀይል፣ የክህሎት፥ የበጀትና የተጠናከረ የመረጃ አያያዝ ትልቅ ሚና ስላላቸው የመንግስት፣ የዓም አቀፍ ተቋማት ፣የሲቪልና የሲቪክ ማህበራት ቅንጅታዊ ስራ የሚኖረው ፋይዳ በእጅጉ ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።

‎በዛሬው ዕለት ይፋ የተደረገው ፕሮግራምም መሠል ችግሮችን ለመቅረፍ ከማገዙም በላይ የስርዓተ ፆታ ድርጅቶችን ተቋማዊ አቅምን በማጠናከር የስርዓተ ፆታ አካቶ ትግበራን ዘላቂና ውጤታማ ማድረግ የሚያስችል ጠንካራ አቅም መገንባት ያስችላል ብለዋል። ፕሮግራሙ ከአውሮፓ ህብረት እና ከስፓኒሽ ኮርፖሬሽን በተገኘ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ የገንዘብ ድጋፍ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከ ዩ ኤን ውመን እና ከአለም የስነ ህዝብ ድርጅት ጋር በመተባበር ለቀጣይ ሶስት አመታት በአማራ፣ ትግራይ፣ አፋር፣ ጋምቤላና ሶማሌ ክልሎች የሚተገበር ይሆናል።
‎ ፕሮግራሙ ውጤታማ ሆኖ በቀጣይ በቀሪዎቹ የአገራችን ክልሎችም እንዲተገበርና በዜጎች ህይወት ላይ ተደማሪ ለውጦችን እያስመዘገቡ ለመሄድ እንዲቻል ዛሬ ይፋ የሆነው ፕሮግራም የሚተገበርባቸው ክልሎች ለፕሮግራሙ ስኬታማነት በሃላፊነት ስሜት በቅንጅትና በቁርጠኝነት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

Please follow and like us: