Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
መንግሥት የሴት ልጅ ግርዛትን እና ያለ ዕድሜ ጋብቻን ለማስቆም ስትራቴጂካዊ ትግበራዎችን ተፈፃሚ በማድረግ ላይ እንዳለ ተጠቆመ
ይህ የተገለፀው የሴት ልጅ ግርዛትና ያለዕድሜ ጋብቻ ለማስወገድ የተዘጋጀውን የአምስት አመት ፍኖተ ካርታ (Road map) አፈጻጸም ጥናት ውጤት ለክልል ባለድርሻ አካላት ይፋ ለማድረግ እና የሁለተኛ ምዕራፍ ፍኖተ ካርታ የድርጊት መርሃ-ግብር አካሄድ ላይ ውይይት በተካሄደበት ወቅት ነው።

በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶች እና ህፃናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት ክብርት ሒክማ ከይረዲን እንደገለፁት እንደ ሀገር ባለፉት አምስት አመታት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት የሆኑትን የሴት ልጅ ግርዛትና ያለዕድሜ ጋብቻን ለመከላከልና ለማስቆም ከግንዛቤና ንቅናቄ ስራዎች ጎን ለጎን ለቀጣይ ለውጥ አምጪና ተጨባጭ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል። ለዚህም መንግሥት የሴት ልጅ ግርዛትን እና ያለ ዕድሜ ጋብቻን ለማስቆም ስትራቴጂካዊ ትግበራዎችን ተፈፃሚ በማድረግ ላይ እንዳለ ጠቁመዋል። መንግስት ያለዕድሜ ጋብቻን እና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም ብሔራዊ ጥምረት (National Alliance) በማቋቋም ወደ ስራ መግባቱን አስታውሰው በዚሁ መሠረትም ብሔራዊ ጥምረቱን በማስተባበር ችግሩን ከመሰረቱ ለማስወገድ በአምስት ውጤቶች ላይ በመስራት ላይ እንደቆየም ጠቅሰዋል። ታዳጊ ሴቶችና ቤተሰባቸውን ማብቃት፣ የማህበረሰብ ተሳትፎን ማሳደግ በተለይ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ጎሳ መሪዎች፣ ታዳጊ ሴቶች ከጥቃት እንዲጠበቁ ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ የተሻለ የህግና የፖሊሲ አፈጻጸም እንዲኖር መስራትና የተሻሻለ የመረጃና የሪፖርት ስርዓት መፍጠር የሚያስችሉ ግቦችን በማስቀመጥ የበጀት ድጋፍ የተደረገበት ሀገራዊ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ሲተገብር መቆየቱን ጠቁመዋል።

ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመዋጋት ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከኃይማኖት አባቶች በተጨማሪ በተሰሩ ቤተሰብ ተኮር እና ማህበረሰብ አቀፍ ስራዎች ይበል የሚያስብሉ መሻሻሎች ቢኖሩም ነገር ግን እንደ ሀገር ከያዝነው ችግሩን ዜሮ የማድረስ ራዕይ ጋር ሲነፃፀር ለቀጣይ ከፍተኛ እና እልህ አስጨራሽ ጥረቶች ያስፈልጋሉ ሲሉ ተደምጠዋል። በተጨማሪም እንደ ክልል በጥናቱ የተለዩ ክፍተቶች ላይ ይበልጥ ትኩረት በማድረግ፣ የቀጣይ ስራዎችን መስራት እንደሚገባ እንዲሁም ጠንካራ ተብለው የተለዩትን ውጤቶች ደግሞ ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል። በውይይቱ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትና ጥሪ የተደረገላቸውን እንግዶችን በማሳተፍ የቀጣይ አቅጣጫ በማስቀመጥ ተጠናቋል
