የአሰራርን ስርዓትንና መመሪያዎችን ማዘመንና ማሻሻል አፈፃፀምን የላቀ ለማድረግ አስፈላገውን ድርሻ ይወጣል ተባለ

ይህ የተገለፀው በከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔትና ስራ ፕሮጀክት የልዩ ድጋፍ አገልግሎት ንዑስ ፕሮጀክት የአገልግሎት አሰጣጥ መመሪያ ለማሻሻል የተዘጋጀ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ ነው።

በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ እንደገለፁት መመሪያውን ማሻሻል ውሎና አዳራቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ የህብረተሰብ ክፍሎችን አገልግሎት አሰጣጥና ተደራሽነትን አንድ እርምጃ በመውሰድ አፈፃፀምን የላቀ ያደርጋል ብለዋል። በመሆኑም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ውሎና አዳራቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የከተማ ልማታዊ የሴፍቲኔት ስራ ፕሮጀክት የልዩ ድጋፍ አገልግሎት ንኡስ ፕሮጀክት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እየተገበረ እንደሚገኝ አስታውሰዋል።በዚህ ፕሮጀክትም በሀገራችን የተለያዩ ከተሞች ውሎና አዳራቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ የህብረተሰብ ክፍሎችን የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ለማሳደግ እንዲቻል በዚህ ዘርፍ ከሚሰሩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር ውል በመግባት እና ዜጎችን ከጎዳና ላይ በማንሳት ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ እና ወደ ቤተሰቦቻቸውና ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ እንዲዋሃዱና ራሳቸውን ችለው መኖር እንዲችሉም እየተሰራ ነው ብለዋል።

ይሁን እንጂ ውሎና አዳራቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የልዩ ድጋፍ አገልግሎት ንዑስ የፕሮጀክቱን የአገልግሎት አሰጣጥ መመሪያ ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት ይህ የግብዓት ማሰባሰቢያ የምክክር መድረክ መዘጋጀቱን ገልፀዋል። ስለሆነም የተዘጋጁትን የአገልግሎት አሰጣጥ መመሪያ ተሻሽሎ ስራ ላይ ለማዋልና ተፈፃሚ ለማድረግ የፌዴራል፣ የክልል እና ከተማ መዋቅሮች፣ የቁልፍ ባለድርሻ አካላት የወቅቱን ፍላጎትና ጥያቄ መመለስ የሚችል ዘመን ተሻጋሪ ግብዓት በመስጠት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል ።

Please follow and like us: