‎ከጾታዊ ጥቃት የጸዳችና ለሴቶች የምትመች ሀገር ለመፍጠር ሁሉም በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ ተገለፀ

‎አለም አቀፉ የፆረ – ፆታዊ ጥቃት ቀን የንቅናቄ የማጠቃለያ መርሐግብር በስካይላይት ሆቴል በተለያዩ ዝግጅቶች እየተካሄደ ነው።

‎የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ባስተላለፉት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት፤ ጾታዊ ጥቃትና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በሴቶችና ህጻናት ውስብስብና ድርብር ለሆኑ ችግሮች እንደሚዳርጉ ተናግረዋል። ‎ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላም በተጎጂዎች ስነልቦና ላይ ጥሎት የሚያልፈው ጠበሳ በቀላሉ የሚሽር አይደለም ብለዋል። የጥቃትን አመለካከትም ሆነ ድርጊቱን አጥብቆ ማውገዝ ብቻ ሳይሆን ጥቃትን አስቀድሞ ለመከላከልና ሙሉ በሙሉ ለማስቆም በጋራ መረባረብ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡ ‎ለሴቶችና ህፃናት ድርብርብና ውስብስብ ችግሮች መንስኤ የሆነው ጾታዊ ጥቃት የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የሕብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግና ለመደገፍ እንዲቻል ለ16 ተከታታይ ቀናት መካሄዱንና ስኬታማ እንደነበረም ገልፀዋል።

‎ለንቅናቄው መርሐግብር ስኬታማነት በማስተባበርና በመምራት ጉልህ አስተዋፅዖ ላበረከቱ የፌዴራልና የክልል አስፈፃሚ አካላት እንዲሁም በተለያየ አግባብ ሲደግፉ ለነበሩ ባለድርሻና አጋር አካላት ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል። ሚኒስቴሩ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርስ ጥቃት እንዲቆም፣ ለሰብአዊ መብት ጥሰት የተጋለጡ ሴቶች ተገቢውን ፍትህ እንዲያገኙ እንዲሁም ተጎጂዎች አስፈላጊውን የማህበራዊና የስነ-ልቦናዊ ድጋፍ እንዲመቻችላቸው በቅንጅት ይሰራል ብለዋል፡፡ ‎በ16ቱ የንቅናቄ ቀናት የተሰሩ ስራዎችን በመደበኛ ጊዜም የበለጠ አጠናክሮ በመቀጠል ከጾታዊ ጥቃት የጸዳችና ለሴቶች የምትመች ሀገር ለመፍጠር ሁሉም በቁርጠኝነት ሊረባረብ ይገባል ብለዋል።

Please follow and like us: