Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የህፃናት መብትና ደህንነት በማስጠበቅ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተመላከተ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ከኢፌዴሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የቅድመ ልጅነት ፕሮግራም ስልጠና ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በሆሳዕና ከተማ እየተሰጠ ይገኛል።
የቢሮው ምክትልና የህፃናት ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ አምሪያ ስራጅ እንደገለጹት የህፃናት መብትና ደህንነት በማስጠበቅ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በቅንጅት መስራት ይገባል ብለዋል። የህፃናት መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረው በክልሉ በየደረጃው የህፃናት መብትና ደህንነት የሚያስጠብቁ አደረጃጀት በመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል። የህፃናት ቅድመ ልጅነት ብሩህ ማድረግ የነገ ዕድገታቸውን አስተዋፅኦ የጎላ ነው ብለው ቀዳማዊ ልጅነት የዕድሜ ክልል የህፃናት ሁለንተናዊ እድገታቸው የሚወሰንበት በመሆኑ ትኩረት መስጠት ይገባል ብለዋል። ተቋማት ለህፃናት ዕድገት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የህፃናት አእምሯዊና አካላዊ ዕድገት ጤናማ እንዲሆን የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል። የኢፌዴሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የህፃናት መብት ጥበቃ መሪ ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ዘቢደር ቦጋለ ትውልድ የሚያስቀጥሉ ህፃናት ላይ መስራት ሀገር ላይ መስራት ነው ብለዋል።

ህፃንነት ከጽንስ እስከ 18 ዓመት መሆኑን ተናግረው በተለይ እስከ 6 ዓመት የህፃናት ሙሉ አእምሯዊና አካላዊ ዕድገት መሰረት በመሆኑ ትኩረት መስጠት እንደሚገባም አሳስበዋል። ነገ የምንጠብቃትን ያደገችና የበለፀገች ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ ዛሬ ህፃናት ላይ የምንሰራው ስራ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።የስልጠናው ተሳታፊዎችም በህፃናት ዕድገት ላይ አበርክቶ ያላቸው በመሆናቸው ለህፃናት ምቹ ከባቢ በመፍጠርና የስርዓተ ምግብ ስርዓት በማሻሻል የህፃናት መቀንጨርን መከላከል እንደሚገባ ተናግረዋል።
ስልጠናው በህፃናት የቅድመ ልጅነት ዘመን ዕድገትና ትምህርት ፖሊሲ፣ የህፃናት መንከባከቢያና ማዕከላት ማቋቋሚያ መስፈርት እና አሰራርን ለመወሰን የወጣ መመሪያ 1084/2017 እና በሌሎች ርዕሶች ላይ ለሁለት ቀናት የሚሰጥ መሆኑ ተገልፆል። በስልጠናው መድረክ ላይ ከክልል፣ከዞንና ከልዩ ወረዳ የተውጣጡ የሴቶች ህፃናት ፣ጤና ፣ ትምህርት ፣የከተማ ልማት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ መሆናቸውን የክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል።
