ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀንን በብሔራዊ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ አከበረች

ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ ለ25ኛ ጊዜ “ታላቁ ታሪኬ፣ ባህልና ልማት በሚል መሪ ቃል፣ እንዲሁም በሀገራችን ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ “ፍልሰተኞችን እናክብር፣ የወደፊት ህይወታቸውን በጋራ እንቅረፅ” በሚል መሪ ቃል ተከብሮ ዋለ::

የዕለቱ የክብር እንግዳ የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በዜጎች ላይ የሚያደርሰውን ስቃይ ለማስቆም መንግሥት “ሁለገብ አቀራረብ” (multi-pronged approach) በመከተል የአዘዋዋሪዎችን መረብ ለመበጠስ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል። ኢትዮጵያ የስደተኞችን መብትና ደኅንነት በማስከበር ረገድ ያላትን ዓለም አቀፍ ሚና አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልፀው መንግሥት በዜጋ ተኮር ፖሊሲው በተለያዩ ሀገራት በችግር ላይ የሚገኙ ዜጎችን በክብር ወደ ቤታቸው የመመለስና የማቋቋም ሥራን ቀዳሚ ትኩረቱ አድርጓል። እኛ ስደተኞችን የችግር ምንጭ ሳይሆን የሀገራትን ኢኮኖሚ የሚያጠናክሩ እና ማኅበረ ባህላዊ ትሥሥርን የሚያጎለብቱ የፈጠራ፣ የስኬትና የለውጥ ኃይሎች አድርገን በማየት ተገቢውን ከለላና ድጋፍ በመስጠት በዓለም አቀፉ የስደተኞች ስምምነት ትግበራ ላይ ግንባር ቀደም ሚናዋን እየተወጣች እንደምትገኝ ገልፀዋል።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ስደት የተሳካና በክብር የሚመራ ሲሆን ለሀገር ልማትና ለባህል ልውውጥ ያለውን ፋይዳ ትልቅ መሆኑን ገልፀዋል ። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ከዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM) ጋር በመተባበር የስደተኞችን መብት ለማስከበርና ህገ-ወጥ ስደትን ለመቀነስ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ በ2025 በአፍሪካ ደረጃ የተጀመረውን “ስለ ስደት የራሳችንን እውነት እንናገር” የሚለውን ንቅናቄ የተቀላቀለች መሆኑን አስታውሰው ከዚህ ጋር በተያያዘም የኢትዮጵያ “የአረንጓዴ አሻራ” መርሃ ግብር በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰትን ስደት ለመከላከልና ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ትልቅ መፍትሔ መውሰዱን ተናግረዋል። ሚኒስቴር መስሪያቤቱ “ብሔራዊ የስደት ኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ” ይፋ ማድረጉን አስታውሰው ይህ ስትራቴጂ በተለይም በገጠራማው የሀገሪቱ ክፍሎች ስላለው ህገ-ወጥ ስደት ግንዛቤን ለማሳደግና ህጋዊ የሥራ ስምሪት አማራጮችን ለማሳወቅ ያለመ ነው። በቀጣይም ኢትዮጵያ የስደተኞችን መብት ከማስከበር ባለፈ፣ ተመላሽ ዜጎች በኢኮኖሚና በሥነ-ልቦና ራሳቸውን እንዲችሉ የሚያደርገውን የ “MPRR” ፕሮግራም አጠናክራ እንደምትቀጥል አመላክተዋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ አጠቃላይ የፍልሰት አስተዳደር ሂደት ዙሪያ የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታዋ ክብርት ሁሪያ አሊ ማብራሪያ አቅርበዋል ። በዕለቱ በስደት አስተዳደር፣ በተመላሾች ድጋፍ እና በዲያስፖራ ተሳትፎ ዘርፍ ከፍተኛ ስኬት ላስመዘገቡ ግለሰቦችና ተቋማት የተሰጠው “የስደት ሻምፒዮናዎች” (Champions of Migration) ሽልማት ነው። ሽልማቱ በዘርፉ ያሉ በጎ ተሞክሮዎችን ወደ ተቋማዊ አሠራር ለመቀየርና ለሌሎች አርአያ እንዲሆኑ ለማድረግ የታለመ መሆኑን ተገልጿል ። ለበዓሉ መሳካት የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ ላደረገው የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM) ለአውሮፖ ህብረት እና ለሌሎች አጋር አካላት ምስጋና የቀረበ ሲሆን በመድረኩ ላይ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች እና በስደት ዙሪያ የሚሰሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተገኝተዋል።

Please follow and like us: