Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የሴቶችን ኢኮኖሚ አቅም ለማሳደግ በሚደረገው ሀገራዊ እንቅስቃሴ የሁሉም ባለድርሻ አካላትና የኢኮኖሚ ልማት ተቋማት ጋር የጠበቀ ትስስር መፍጠር ሀገራዊ ፋይዳው የላቀ መሆኑ ተገለፀ።
የሴቶች የኢኮኖሚ አቅም ለማሳደግ በሚደገው ሀገራዊ እንቅስቃሴ የሚገጥሙ እንቅፋቶችን በቅንጅት ለመፍታት ቁልፍ ድርሻ ካላቸው የኢኮኖሚ ልማት ተቋማት ጋር የጠበቀ ትስስር ፈጥሮ በጋራ መንቀሳቀሱ አዋጭና የሚኖረውም ሀገራዊ ፋይዳው የላቀ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገልፀዋል ።
ይህ የተገለፀው በሚኒስቴር መ/ቤቱ አስተባባሪነትና ዩ ኤን ውመንና አክሽን ኤድ ኢትዮጵያ ቅንጅት በተዘጋጀው 4ኛው ሀገር አቀፍ የሴቶች ኢኮኖሚ ማብቃት ፎረም ላይ ነው። የተቀናጀ ብዙሀኑን ሴቶች ተጠቃሚ የሚያደርግ ብሎም ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስትራቴጂ መንደፍ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ሚኒስቴር መ/ቤቱ በፅኑ እንደሚያምን ተናግረዋል። የ2030 የዘላቂ ልማት ግቦች አጀንዳን ለማሳካት የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ አንዱና ቁልፍ ተግባር መሆኑን አስታውሰው ይህን ዓለም ዓቀፍ አጀንዳ ከግብ ለማድረስ በሁሉም ዘርፎች ሴቶችን ማበረታታት፣ መብታቸውን ማክበር እና ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል ። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ልዩ ልዩ ፍትሀዊ ያልሆኑ ጉዳዮችንና አሰራሮችን በመቅረፍ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማጎልበትና የስራ አጥነት ችግርን ከመቅረፍ አኳያ በተለይም በክህሎት፣ በፋይናንስ፣ በመስሪያ ቦታና የገበያ ትስስር በመፍጠር ረገድ ያሉባቸውን ተግዳሮቶች ደረጃ በደረጃ ለማቃለል የሚያስችሉ የግንዛቤና ንቅናቄ ስራዎችን በስፋት እየሠራ መሆኑን ገልፀዋል።
ነገር ግን ከነዚህ ስራዎች ባሻገር ተጨባጭ ስራዎች በገቢና የስራ ዕድል ፈጣሪ ተቋማትን በማስተባበር፣ ከቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት ጋር በመቀናጀትና አስፈላጊውን ስልጠና እንዲያገኙ በማመቻቸት እንዲሁም የፋይናንስ ተቋማት ለሴቶች ተስማሚ የሆነ የብድር አቅርቦት ስርዓትና የተለያዩ ዲጂታል ሞዴሎችን እንዲዘረጉና በተቋማት መካከል ቅንጅታዊ አሰራር እንዲጎለብት በማስቻል በኩል ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል። በከተማም ሆነ በገጠር ያሉ ሴቶችን ችግር ለመፍታት ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ማጎልበት ዋነኛው መፍትሔ መሆኑን ገልፀው ይህም የሁሉም አካላትን ቅንጅት የሚጠይቅ እንጂ ለመንግስት ብቻ የሚተው አለመሆኑን ጠቁመዋል።
ፎረሙም የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማጎልበት አንጻር ከአገልግሎት ተደራሽነት ጋር ያሉ ክፍተቶችና መፍትሄዎቻቸው፣ ፈታኝ ጉዳዮች እና ዕድሎች፤ ስልትና መፍትሄዎች የምንቀይስበት፣ አቅጣጫ የምናመላክትበት እንዲሁም ለላቀ ውጤት በሚያበቁ ነጥቦች ዙሪያ የጋራ መግባባት ላይ የሚደረስበት እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል ። በዕለቱም በጥቃቅንና ንግድ ላይ የተሠማሩ ሴቶች ስራዎቻቸውን ያቀረቡበት ኤግዚብሽን ጎን ለጎን ተካሂዷል።
