Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የህጻናት ጥበቃ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እየተካሄደ ነው
በመድረኩ የሚመለከታቸው የፌዴራል ተቋማት እና አጋር አካላት እንዲሁም ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደር የተውጣጡ የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ያሳተፈ በህፃናት ጥቃትን መከላከልና ምላሽ መስጠት ላይ ያተኮረ የግንዘቤ ማስጨበጫና የተሞክር ልውውጥ መድረክ ነው፡፡
የህጻናት መብትና ጥበቃ መሪ ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ዘቢደር ቦጋለ በመክፍቻ ንግግር እንደገለፁት፥ በተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ክስተቶች ምክንያት ህጻናት ለጉልበት ብዝበዛ፣ ለጎዳና ተዳዳሪነት፣ ለህገ ወጥ ፍልሰት፣ ለጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ጥቃት፣ ደህንነት ባልተጠበቀ የበይነ መረብ አጠቃቀም የሚደርሱ ጥቃቶች፣ለጾታዊ ትንኮሳና ተያያዥ ጥቃቶች የሚጋለጡበት አጋጣሚ የሰፋ መሆኑን ተናግረዋል። በተጨማሪም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋና አለም አቀፋዊ ችግር እየሆነ የመጣው ደህንነቱ ያልተጠበቀ የበይነ መረብ አጠቃቀም በህፃናት ትምህርት አቀባበልና ውጤታማነት፣ በጤናና እክል ፣የማህበራዊ ተግባባት መቀነስ ብሎም ለአስከፊ ጥቃቶች፣ በስነ-ልቦና ጫናና ሁለንተናዊ ስብዕና ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ተናግረዋል። ህፃናት የሚገጥማቸውን ችግሮች አስቀድሞ ከመከላከል ጎን ለጎን ዘላቂ መፍትሔ በማበጀት መብትና ደህንነታቸውን ለማስጠበቅና ትውልድን ለመታደግ ከሴክተሩም ሆነ ከባለድርሻ አካላት ብዙ መስራት ይጠበቃል ብለዋል።
በህጻናት ደህንነትና ጥበቃ እንዲሁም በበይነ መረብ አጠቃቀም ዙሪያ ራሳቸው ህፃናትን ጨምሮ ቤተሰብን፣ መምህራንን፣ ተማሪዎችና ማህበረሰቡን በሰፊው ማስገንዘብና ማንቃት መፍትሔ መሆኑን አመላክተዋል። በዚህ ረገድ ሚኒስቴሩ ከቻይልድ ፈንድ ኢትዮጵያ፣ ከዩኒሴፍና ሌሎች የልማት አጋራት ጋር በመተባበር በህፃናት ጥበቃ ላይ ያተኮሩ የተለያዩ የአሰራር ማዕቀፎችንና ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ በስራ ላይ ማዋሉን ገልፀዋል። በፌዴራል ደረጃ የተጀመሩ ስራዎችን ወደ ታች በማውረድ እና አጠናክሮ በማስቀጠል የሚጨበጥ ውጤት ለማስመዝገብ መረባረብ ያስፈልጋል ብለዋል። ሀገራዊና ተቋማዊ ጥረቱ እንዲሰምርም በየዘርፉ የተሰማሩ ባለድርሻና አጋር አካላት ልዩ ትኩረት እንዲሰጡና በቅንጅት እንዲሰሩም ጠይቀዋል።
