የሴት አይነ-ስውር ምሁራን በፖሊሲ ቀረጻዎች ላይ በመሳተፍ ሀገራችን የጀመረችውን አካታች የብልፅግና ጉዞ ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

የኢትዮጵያ ምሁር አይነ-ስውራን ሴቶች ማህበር አማካይነት የብሬል ቀን በትላንትናው ዕለት ተከብሮ ውሏል ።

በዕለቱ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ ብሬል ለአይነ ስውራን ንባብና ጽሁፍ ባዘለል ለአይነ ስውራን ነጻነት፣ ክብርና ራስን መቻል እንዲሁም መሠረታዊ የሰብአዊ መብቶችን ለማስከበር የሚረዳ ታላቅ መሣሪያ ነው ሲሉ ገልፀዋል ። ሀገራችን ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት የሴት አይነስውር ምሁራን ዕውቀትና ልምድ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል። በተለይም በፖሊሲ ቀረጻዎች ላይ በመሳተፍ ሀገራችን የጀመረችውን አካታች የብልፅግና ጉዞ ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉና ለአካል ጉዳተኛ እህቶችም ድምጽ በመሆንና በምርምር ስራዎች መፍትሄዎችን በማፍለቅ በኩል የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም አካል ጉዳተኞችን ማካተት የፍትህ ጉዳይ መሆኑን በጽኑ በማመን የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው የብሬል ተደራሽነትን ማስፋፋት፡ በትምህርት ተቋማትና በሕዝብ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች የብሬል ጽሁፎች እንዲስፋፉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራን ይገኛል ብለዋል።

ይህም ብሬልን እንደ ተራ የመገናኛ ዘዴ ሳይሆን፣ አካል ጉዳተኞችን በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካዊ መስኮች እኩል ተሳታፊ ለማድረግ እንደሚያስችል ቁልፍ መሳሪያ ያደርገዋል ብለዋል። በተጨማሪም የብሬል ጽሁፍ ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ጋር ተቀናጅቶ (Refreshable Braille Displays) ተደራሽ እንዲሆን ድጋፍ ማድረግን ጨምሮ ምቹ የሥራ አካባቢ፡ በሥራ ቅጥርና በሥራ ቦታዎች ላይ የሚታዩ መድልዎችን ለማስቀረት የሕግ ማዕቀፎችን የማሻሻልና የማስፈጸም ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል። ማህበሩ እያከናወነ ያለውን የሚያበረታታ ተግባር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቅርበት እንደሚደግፍና እንደሚያበረታታ ገልፀዋል። የኢትዮጵያ ምሁር ዐይነ ሥውራን ሴቶች ማኅበር በ2014 ዓ.1ም የተመሠረተ ሲሆን በውስጡ የመጀመሪያ ዲግሪና ከዚያ በላይ የትምህርት ደረጃ ያለውን በዕውቀታቸውና በክህሎታቸው ራሳቸውን የለወጡና ማኅበረሰባቸውን ለማገልገል የቆረጡ አባላትን የያዘ ነው።

Please follow and like us: