ሴቶችና ህፃናት አስተማማኝ፣ አካታችና ፍትሃዊ በሆነው የፋይዳ ምዝገባ ስርዓት ውስጥ እንዲያልፉና ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ በቅንጅትና በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

‎የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም 2ኛው ዙር “ፋይዳ ለኢትዮጵያ” የንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረክ በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
‎‎የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም አስተባባሪ ጋር በመተባበር በተዘጋጀው የንቅናቄ መድረክ የሲዳማ፣ የማዕከላዊ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተውጣጡ የሴት አደረጃጀቶች እየተሳተፉ ይገኛል። ‎በመድረኩ ላይ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ በመንግስት የሚሰጡ ሁለንተናዊ አገልግሎቶችን በቀላሉና በፍጥነት ተደራሽ በማድረግ ሴቶችና ህፃናት የሚደርስባቸውን ጫናና ተፅዕኖ ለማስቀረት ያግዛል ብለዋል። በየክልሉ ፋይዳን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ውጤታማ እንዲሆን የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርጉ አፅዕኖት ሰጥተዋል።

‎የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ዘርፍ ክብርት ሒክማ ከይረዲን በበኩላቸው፥ ሴቶችና ህፃናት እንደዜጋ በህግ ፊት የመታወቅ፣ የመሳተፍና ተጠቃሚ የመሆን መብት አላቸው ብለዋል። ዲጂታል መታወቂያ የምዝገባ ስርዓት ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም ሴቶች፣ ህፃናትና ልዩ ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን ሰብዓዊ መብት ለማስከበር፣ የስርዓተ ፆታ እኩልነትን ለማስፈንና በየዘርፉ ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አስተዋፅዖው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል። እቅዱን እስከታች በማውረድ ሴቶችና ህፃናት አስተማማኝ፣ አካታችና ፍትሃዊ በሆነው የፋይዳ ምዝገባ ስርዓት ውስጥ እንዲያልፉና የላቀ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ በቅንጅትና በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

‎‎የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና አስተባባሪ ዮዳሔ አርዓያሥለሴ በበኩላቸው፥ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ኢትዮጵያ ለያዘችው የዲጂታል ኢኮኖሚ ስርዓት ግንባታ ስኬት ቁልፍ ሚና ይጫወታል፤ ለዚህም መንግስት በዚህ አመት 90 ሚሊዮን ዜጎችን የፋይዳ ተጠቃሚ ለማድረግና ከተለያዩ አገልግሎቶች ጋር ለማስተሳሰር በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል። ሀገራዊ ግቡ እንዲሳካም ሁሉም በጋራ እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል።
‎

Please follow and like us: