ሴቶችን ማደራጀት ብቻውን የመጨረሻ ግብ አይደለም፤ ተቋማዊ አደረጃጀቱ ለሴቷ ትርጉም ያለው አበርክቶ እንዲኖረው ለማስቻል በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል

‎ሴቶች በልማት፣ በዴሞክራሲና በመልካም አስተደደር ረገድ የሚስተዋሉ የጋራ ችግሮችን በተደራጀ አኳኃን መፍታትና የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንዲችሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሴቶች የልማት ህብረትን ጨምሮ የተለያዩ የሴት አደረጃጀቶች ተቋቁመው በርካታ ውጤታማ ስራዎችን እየሰሩ መሆኑን የሴቶችና ህፃናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሒክማ ከይረዲን ገልፀዋል።

‎ሴቶች ሰፊውን የማህበረሰብ ክፍል የሚሸፍኑ ቢሆንም በእነዚህ አደረጃጀት የታቀፉ ሴቶች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታ ገልፀው ያልታቀፉ ሴቶች እንዲካተቱ በማድረግ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸው በተጨባጭ እንዲረጋገጥ በጋራ መሰራት ይኖርበታል ብለዋል። ሴቶችን ማደራጀት ብቻውን የመጨረሻ ግብ አይደለም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ተቋማዊ አደረጃጀቱ ለሴቷ ትርጉም ያለው አበርክቶ እንዲኖረው ለማስቻል በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። የልማት ህብረትን ጨምሮ በየአካባቢው የተቋቋሙ የሴት አደረጃጀቶች ጠንካራ አቅም በመፍጠር የአባላትን ሁለንተናዊ መብትና ተጠቃሚነት ከማስጠበቅ ባለፈ ሀገራዊና ተቋማዊ ተልዕኮን በብቃት መፈፀም ከሚችሉበት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ በቅንጅት መረባረብ ይገባል ብለዋል።

‎‎በዚህ ረገድ የሴት አደረጃጀቶች ፎረም ሚና የላቀ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት የሚያግዙ የግንዛቤና ንቅናቄ ተግባራትን ከማካሄድ ጎን ለጎን ቅንጅትና ትብብርን በማጠናከር፣ በማብቃት፣ በማስተባበርና በመደገፍ የድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ከሴት አደረጃጀቶች ፎረም እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን እንደሚሰራና አስፈላጊውንም ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

Please follow and like us: