Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
በሴት ልጅ ግርዛትና ያለ እድሜ ጋብቻ ላይ በተሰሩ ስራዎች እንደ ሀገር ውጤት መምጣቱ ተገለፀ
አለም አቀፉ የሴት ልጅ ግርዛት ያለመታገስ ቀን በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በአሶሳ ከተማ በተለያዩ መርሐግብሮች እየተከበረ ይገኛል።
በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችና ህፃናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ በዕለቱ እንደገለፁት፥ የሴት ልጅ በሴቶችና ህፃናት ላይ ከፍተኛና ተደራራቢ ችግሮችን የሚያስከትል እንዲሁም የሴቶችን ጤና፣ ክብርና ደህንነት በእጅጉ የሚጎዳና አፍላ ህፃናትን ደግሞ ለዘለቄታዊ የጤና ችግርና ለሞት የሚዳርግ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሆኑን ገልፀዋል። ችግሩን ለማስወገድም በየደረጃው ታዳጊ ሴቶችና ቤተሰባቸውን ከማብቃትና ከግንዛቤና ንቅናቄ ስራዎች ባሻገር የማህበረሰብ ተሳትፎን ማሳደግ፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የጎሳ መሪዎችን ማሳተፍ ታዳጊ ሴቶች ከጥቃት እንዲጠበቁ ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል። ሚኒስቴር መ/ቤቱም የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስወገድ የተሻለ የህግና የፖሊሲ አፈጻጸም እንዲኖር ማስቻል በሚሉ ማዕዘኖች ስር ለ5 ተከታታይ አመታት መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በአንድ ብሔራዊ ጥምረት በማምጣትና በማስተባበር እንዲሁም እንደ ሀገር ያለንን ውስን የገንዘብ እና የቴክኒክ አቅም በማቀናጀት ሀገራዊ ፍኖተ-ካርታን በማዘጋጀት ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት በመስራት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በዚህም በሴት ልጅ ግርዛትና ያለ እድሜ ጋብቻ ላይ በተሰሩ ስራዎች እንደ ሀገር ውጤት መምጣቱንም አያይዘው ተናግረዋል።የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክርቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ አስካለች አልቦሮ በበኩላቸው፣ የሴት ልጅ ግርዛት የሴቶችን ሰብአዊ መብትን የሚጥስ ጎጂ ድርጊት በመሆኑ በጋራ ማስቆም ይገባል ብለዋል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አለምነሽ ይባስ በክልሉ ማኅበረሰቡን የማስተማርና የማንቃት ሥራ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የሴት ልጅ ግርዛትን በመከላከል ነጻ ቀበሌዎችን የመፍጠር ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል። በአለም አቀፍ ደረጃ ለ34ኛ ጊዜ እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ9ኛ ጊዜ የሴት ልጅ ግርዛትን ያለመታገስ ቀን ግርዛትን ባለመታገስ “ለሴቶች መብት መከበር በጋራ እንቁም!” በሚል መሪ ቃል በመከበር ላይ ይገኛል።
