Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የሴት ልጅ ግርዛትንና ያለዕድሜ ጋብቻን ለመከላከልና ለማስቀረት ከግንዛቤና ንቅናቄ ስራዎች ባሻገር የሴቶችን ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ አንዱ መሆኑ ተጠቆመ
ይህ የተገለፀው ከሴት ልጅ ግርዛትና ካለዕድሜ ጋብቻ ነፃ የሆነውን በአሶሳ ዞን አብራሞ ወረዳ ነባር ኮመሺጋ ቀበሌ በተጎበኘበት ወቅት ነው።
በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችና ህፃናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት ክብርት ሂክማ ከይረዲን እንዳሉት በሀገራችን በስፋት ከሚፈፀሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መካከል አንዱ የሆነውን የሴት ልጅ ግርዛትን ለመከላከል ከግንዛቤና ንቅናቄ ስራዎች ባሻገር የሴቶች ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሆነ ተናግረዋል። በአሶሳ ዞን አብራሞ ወረዳ ነባር ኮመሺጋ ቀበሌ ከሴት ልጅ ግርዛትና ካለዕድሜ ጋብቻ ነፃ እንዲሆን ሰፊ ስራዎችን በመስራት አስተዋፅኦ ላበረከቱት የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች እውቅናና ምስጋና ሰጥተዋል። ይህ የሚያሳየው የማህበረሰብ ተሳትፎና አጋርነትን በማጠናከር የሴት ልጅ ግርዛትን የማይታገስ ማኅበረሰብ ለመፍጠር እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎችን በተቀናጀ መልኩ ማጠናከር እንደሚገባ የሚጠቁም መሆኑን ገልፀዋል።
ሚኒስቴር መስሪያቤቱም በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ በመቀጠል በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሱ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ሙሉ በሙሉ ከሀገራችን እስኪጠፋ ድረስ በትብብር እንደሚሠራ ቃል ገብተዋል። የቀበሌው የሀይማኖት አባት ሼህ መሀመድ አብዱረሂም እንደገለፁት በቀበሌዋ የተገኘውን መልካም ጅማሮ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀው ሌሎች ወረዳዎችና ቀበሌዎችም ነፃ እንዲወጡ የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን ለማስፋፋት ያላቸውን ተነሳሽነት ገልፀዋል።
