Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የህጻናት ፓርላማ መመስረት ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መጎልበት ጠንካራ መሰረት የሚጥል መሆኑ ተገለፀ
ሀገር አቀፍ የህፃናት ፓርላማ የ2018 በጀት አመት የ6ወር እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት በሁሉም ክልሎች ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የህጻናት መብትና ጥበቃ መሪ ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ዘቢደር ቦጋለ በመክፍቻ ንግግራቸው የህጻናት ፓርላማ መመስረት ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መጎልበት ጠንካራ መሰረት የሚጥል መሆኑ ገልፀዋል። ራሳቸውንም ሆነ አካባቢያቸውን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ የራሳቸው ተሳትፎ መኖሩ መብትና ደህንነተቻውን ለማስጠበቅ የሚደረገው ጥረት ውጤታማ ለማድረግ የበኩሉን እገዛ ያደርጋል ብለዋል። ሃገራችን ኢትዮጵያ ለህጻናት ሁለንተናዊ መብት መከበርና ማህበራዊ ደህንነት መረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አለም አቀፋዊና አህጉራዊ ሰነዶች ተቀብላ ከማጽደቋም ባሻገር ለስምምነቶቹ አፈጻጸምና ስኬታማነት እገዛ የሚያደርጉ በርካታ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎችን እየወሰደች መሆኑን ተናግረዋል። ከህፃናት መብቶች መካከል የመታወቅ መብት አንዱ ነው ያሉት ስራ አስፈፃሚዋ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ሕፃን በዲጂታል ሥርዓት ውስጥ የሚታወቅበትና መብቱ የሚጠበቅበት ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።
የህፃናት ፓርላማ አባላት አምባሳደሮች በመሆን፣ እድሜያቸው ከ5 ዓመት በላይ የሆኑ ሕፃናት በዚህ ሥርዓት ተመዝግበው ህጋዊ ማንነታቸውን እንዲያረጋግጡ ግንዛቤ መፍጠር ይጠበቅባችኋል በማለት አስገንዝበዋል። የክልል የህፃናት ፓርላማ ፣ የክልል የህፃናት ፓርላማ የ6 ወር አፈፃፀም እና የቀጣይ የ6 ወር ዕቅድ፣ በህፃናት ላይ በበይነመረብ አማካኝነት የሚፈፀም ጥቃትን በመከላከል ላይ ያተኮረ ስልጠና እና የፋይዳ መታወቅያ ለህፃናት ያለውን ጠቀሜታ በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። በመርሀ-ግብሩም ከሁሉም ክልሎች እና የሁለቱ ከተማ አስተዳደር የህፃናት ፖርላማ አፈጉባኤ፣ ም/አፈጉባኤ፣ ጸኃፊዎች እና የሴክተር ህፃናት መብት ጥበቃ ዳይሬክተሮች ተገኝተዋል።
