Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ጀግና ሴት የመከላከያ ሰራዊት አባላት የፅናት፣ የቁርጠኛነት እና የአይበገሬነት ተምሳሌት ናቸው
አለም አቀፉ የሴቶች ቀን “ሴት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ሰላምን ለማስጠበቅና ለማፅናት” በሚል መሪ ቃል በኢፌዴሪ የመከላከያ ሚኒስቴር በእውቅና በተለያዩ መርሐግብሮች ተከብሯል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፥ የሴቶች መብትና እኩልነትን ለማስጠበቅ በየዘመናቱ ሰፊ ትግል ሲካሄድ መቆየቱን አስታውሰዋል። ከለውጡ ወዲህም በመንግስት እየተወሰዱ ባሉ ጠንካራ እርምጃዎች ሴቶች በየዘርፉ ያላቸው ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን እና ለተጀመረው የብልፅግና ጉዞ መፋጠን ደማቅ አሻራቸውን እያሳረፉ ይገኛል ብለዋል። ጀግና ሴት የመከላከያ ሰራዊት አባላት የፅናት፣ የቁርጠኛነት እና የአይበገሬነት ተምሳሌትና ማሳያ መሆናቸውን ተናግረዋል። በፈፁም ጀበድ እውቅና የተሰጣቸውን ሴት ጀግኒቶችንም እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል። ሴት አባላትም ከወንድ ጎዶቻቸው ጋር በመሰለፍ የሚገጥሟቸውን ፈታኝ ሁኔታዎችን ሁሉ በጀግንነት እና በፅናት በማለፍ በየተሰማሩበት የስራ መስክ ሁሉ ውጤታማ በመሆናቸው እንኮራባቸዋለን፤ ሊመሰገኑም ይገባቸዋል ብለዋል።
ሴቶችን ማብቃት ሃገር መገንባት መሆኑን የጠቀሱት ክብርት ሚኒስትሯ የሴቶችን መብትና እኩልነት ለማረጋገጥ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንዲሚቀጥልና ለጀግናው መከላከያ ሰራዊት የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል። የኢፌዴሪ የመከላከያ ሚኒስትር ክብርት እንጂነር አይሻ መሀመድ በበኩላቸው፥ ሴቶች በአውደ ውጊያ ግንባር የፈፀሙት ገድልና በየተሰማሩበት የሙያ መስክ ያስመዘገቡት ስኬት ሴትነትን ካለመቻል ጋር ያስተሳሰረውን የተሳሳተ አስተሳሰብ በተግባር የገፈፈና የኢትዮጵያ ሴቶች ከአባቶቻቸውና ከእናቶቻቸው የወረሱትን የአይበሬነት መንፈስ ዳግም ያበሰረ ነው ብለዋል።
