Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ሚኒስቴሩ ከስለኔ የሴቶች አቅም ግንባታና የበጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመተባበር ለእዝነት አካል ጉዳተኛ ህፃናትና ወላጆች መርጃ ድርጅት የአፍጥር ፕሮግራም እና የገንዘብ ድጋፍ አደረገ
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ከለውጡ ወዲህ መንግስት ልዩ ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ሰው ተኮር ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

የተለያዩ አካላትን በማስተባበርም የአካል ጉዳት ያለባቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች እና የመንግስትን ሸክም በሚያቀል መንገድ ሰብዓዊ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን ለመደገፍና የዘርፉን እንቅስቃሴ ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ ቢሆንም ከችግሩ ስፋት አኳያ አሁንም ብዙ ስራ ይቀረናል ብለዋል።
እንደ እዝነት ብዙ መሰጠትን፣ ፅናትን፣ ትዕግስትንና ትጋትን በሚጠይቀው ስራ ላይ ለተሰማሩና ለሌሎችም አለኝታ ለሆኑ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ልዩ ክብር አለን ብለዋል። የድርጅቱን ጥረት ለማገዝም ሚኒስቴሩ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ገልፀዋል። ወደፊት አብረን በጋራ እንሰራለን ብለዋል።
እዝነትን ጨምሮ በጎ ስራ እየሰሩ ላሉ መሠል ተቋማት ድጋፍ እያደረጉ ያሉ አካላትን በተጠቃሚ ወገኖች ስም አመስግነዋል። እርስ በእርስ ከተደጋገፍን ማህበራዊ ችግሮቻችን በራሳችን አቅም መቅረፍ፣ የልጆቻችንን ተስፋ ብሩህ ማድረግና የተሻለች ሀገር መፍጠር እንችላለን ያሉት ክብርት ሚኒስትሯ ሁሉም ለበጎ ስራ እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል። የድርጅቱ መስራችና ስራ አስኪያጅ ዘቢባ አህመድ በበኩላቸው፤ በድርጅቱ እየተደገፉ ያሉ ህፃናት በገጠማቸው ተደራራቢ የአካልና የጤና እክል ምክንያት ቤት የተደበቁ፣ ከአይን የራቁና ብዙ ድጋፍ የሚፈልጉ መሆናቸውን እና ለወላጆቻቸውም የስራ ዕድል መፈጠር መቻሉን ገልፀው ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
