‎ሴቶች በየተሰማሩበት መስክ ሁሉ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብና የተጀመረውንም የብልጽግና ጉዞ ከዳር ለማድረሰ በትጋት መስራት ይጠበቅባቸዋል – ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሴት ሰራተኞች ፎረም አባላት አለም አቀፉን የሴቶች ቀን “50 ዓመት የሴቶች ድምጽ ለእኩልነት እና ለበለጸገች ኢትዮጵያ!” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዝግጅቶች አክበረዋል።

‎በዓሉን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው መርሐግብር ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ፥ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ለመብትና እኩልነት መከበር ሰፊ ትግል ማድረጋቸውንና ለተገኘው ውጤትም ጠንካራ መሠረት ጥለው ማለፋቸው አንስተዋል። ሴት ሰራተኞችም የእነርሱን ፈለግ በመከተል ለስርዓተ ጾታ እኩልነት መስፈን ከሚደረገው ርብርብ ጎን ለጎን በየተሰማሩበት መስክ ሁሉ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብና የተጀመረውንም የብልጽግና ጉዞ ከዳር ለማድረሰ በትጋት መስራት ይጠበቅባቸው ሲሉ አስገንዝበዋል። ሴት ሰራተኞችን ለማብቃት እንዲሁም በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በውሳኔ ሰጪነት ረገድ ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል። ፎረሙን ለማጠናከርም በጋራ እንሰራለን ሲሉ ክብርት ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

‎በዕለቱ ባለፉት 50 ዓመታት የኢትዮጵያ ሴቶችን የትግል ጉዞና የተገኙ ውጤቶችን የተመለከተ ሰነድ በፎረሙ አመራር ወ/ሮ ትሁና ስንሻው ቀርቦ ውይይት ተደርጓል። የኢትዮጵያ ሴት ምሁራን አይነስውራን ማህበር መስራት ዶ/ር በቀለች በበኩላቸው የህይወት ተሞክሯቸውን አካፍለዋል።

Please follow and like us: