Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ዓለም አቀፍ የዳውን ሲንድሮም ቀን-“ብቸኝነትን በጋራ እናሸንፋለን!”
ዓለም አቀፍ የዳውን ሲንድሮም (Down Syndrome) ቀን በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ እ.ኤ.አ. ማርች 21 ቀን 2012 እንዲከበር መወሰኑን ተከትሎ የህብረተሰቡን ግንዛቤና ተግባራዊ ምላሽ ሰጪነት በሚያሳድጉ ልዩ ልዩ መርሀ ግብሮች ዕለቱ በየዓመቱ መጋቢት 12 ቀን እየታሰበ የሚገኝ ሁነት ነው፡፡
የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የዳውን ሲንድሮም ቀን መሪ ቃል “ብቸኝነትን በጋራ እናሸንፋለን!” የሚል ነው፡፡
ለመሆኑ የአእምሮ እድገት ውሱንነት ማለት ነው? መገለጫዎቹ፣ መንስኤዎች፣ ሰው ሰራሽ ምክንያቶች፣ የሚያስከትለው ችግሮቹና መፍትሄዎቹስ ምንድን ናቸው?
የአእምሮ እድገት ውሱንነት – የአእምሮ ብስለት ጉልህ በሆነ ልዩነት ከአማካዩ በታች መሆንና የግላዊና ማህበራዊ ክንዋኔዎች ብቃት መጓደል ማለት ነው::
የአእምሮ እድገት ውሱንነት ያለባቸው ህጻናትና ወጣቶች በአእምሮ እድገታቸውና በስሜት ህዋሳታቸው መዳበርና በማህበራዊ ግንኙነቶች ከእድሜ እኩዮቻቸው አንጻር ውሱንነት የሚታይባቸው ናቸው፡፡
የአእምሮ እድገት ውሱንነት መገለጫ ባህሪያት
የመግባባት፣ ራስን የመንከባከብ፣ የአኗኗር የማህበራዊ ክህሎቶች፣ የንብረት አጠቃቀም፣ ራስን የመምራት፣ ለራስ የሚደረግ ጥንቃቄ፣ የቀለም ትምህርቶችን የመማር ውሱንነቶች ሲሆኑ መገለጫቸውም በመኖሪያ ቤት፣ በትምህርት ቤት፣ በመዝናኛና በስራ ቦታ በሌሎች ማህበራዊ መስተጋብሮች በሚከናወኑባቸው ስፍራዎች የሚታይ ውሱንነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ከተለመዱት የዳውን ሲንድሮም አካላዊ ገጽታዎች መካከል የጡንቻ ዝቅተኝነት፣ አጠር ያለ ቁመት፣ ወደ ላይ ሰቀል ያለ አይንና ዝቅ ያሉ ጆሮዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ሰው ሰራሽ ምክንያቶች
የአእምሮ እድገት ውሱንነትን ያለባቸው ዜጎች ቁጥር ከሚያበራክቱ ሰው ሰራሽ ምክንያቶች መካከል የቤተሰብ መፍረስ፣ የወላጆች ወይም የአሳዳጊዎች ቸልተኝነት፣ የአልኮል ሱሰኝነት፣ ያለ ሃኪም ትዕዛዝ የሚወሰዱ መድሃኒቶችና አደንዛዥ ዕጾች ተጠቃሾች ናቸው፡፡
የሚያስከትለው ችግር
ዳውን ሲንድሮም ያለባቸው ሰዎች ከሌሎች ሰዎች እኩል እንዳይታዩ፣ እንደህጻን እንዲያዙ፣ ከብዙ ነገሮች እንዲቆጠቡ፣ ተሳትፎዋቸው እንዲገደብ ከማድረግ ባሻገር ለመገለልና ለጥቃት እንዲጋለጡ ያደርጋል።
መፍትሔው
ዳውን ሲንድሮም ያለባቸው ሰዎች ፍላጎታቸው የተለያዩ እንደመሆኑ መጠን እንደፍላጎቶቻቸው መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው፣ ፍቅርን እንድናጋራቸው፣ ተሰጥኦዎቻቸውን በመለየት እያበረታታን ለስኬት እንድናበቁ ማድረግ ይገባል።
በጥናትና በእውቀት ላይ በተመሰረተ መልኩ ድጋፍና ክብካቤ እንዲያገኙ ማስቻል ያስፈልጋል።
በአጠቃላይ በአንድነትና በመደጋገፍ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተለይም ደግሞ የአእምሮ እድገት ውሱንነት ላለባቸው ዜጎች ልዩ ትኩረት በመስጠት መብቶቻቸውን በዘላቂነት ለማስከበር በጋራ መስራት ከሁላችንም ይጠበቅብናል።
በዚህ ረገድ ዲቦራ ፋውንዴሽንና ፍቅር የኢትዮጵያ የአእምሮ እድገት ውሱንነት ብሔራዊ ማህበር የአእምሮ እድገት ውሱንነት ካለባቸው ዜጎችና ከወላጆቻቸው ጋር በቅንጅት በመስራት የጎላ አስተዋጽዖ በማርከት ላይ የሚገኙ በመሆኑ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በተጠቃሚ ህጻናት ስም የላቀ ምስጋና እያቀረበ ወደፊትም ድጋፋን አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።
ምንጭ ፦ “የአእምሮ እድገት ውሱንነትን መረዳት” በፍቅር የኢትዮጵያ የአእምሮ እድገት ውሱንነት ብሔራዊ ማህበር የተዘጋጀ ቡክሌት
