‎ድንበር ዘለል ትብብርንና ቀጣናዊ አጋርነትን ይበልጥ ለማጠናከር፣ የፍልሰት ተጎጂ ህፃናት ጉዳይ አያያዝን ለማሻሻል እና የተመላሽ ህፃናትን መብት ለማስጠበቅ የሚያስችል ጠንካራ ስርዓት ለመዘርጋት ሚኒስቴሩ ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ክብርት ሁሪያ አሊ ገለጹ

የፍልሰተኛ ህጻናት ጥበቃና ድጋፍን በተመለከተ የምስራቅ አፍሪካ በይነ ልማት ድርጅት(IGAD) ባዘጋጀው የአገልግሎት አሰጣጥ መስፈርት (Standard Operating Procedure for the protection and assistance of children on the move) ሰነድ ላይ የኢጋድ አባል ሀገራት ተወካዮች እና ሌሎች አጋር የሆኑ ድርጅቶች የተሳተፉበት አውደ ጥናት እየተካሄደ ይገኛል።

‎‎በመድረኩ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ ባስተላለፉት መልዕክት በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች፣ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ እንዲሁም በህገ-ወጥ ደላሎች በመታለል በርካታ ህጻናት ድንበር ተሻግረው ወደሌላ ሀገር እንደሚጓዙ ጠቁመዋል። ‎ፍልሰተኛ ህጻናት ለተለያዩ ጥቃቶች፣ ለጉልበት ብዝበዛ፣ ለአካላዊ ጉዳት፣ ለከፋ ችግር እየተዳረጉ መሆኑን ገልፀው መደበኛ ያልሆነ የህጻናት ፍልሰትና ስደትን ለመግታት እና መብታቸው ለማስጠበቅ ድንበር ዘለል ትብብርንና ቀጣናዊ አጋርነትን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ ክብርት ሁሪያ አሊ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ችግሩን ለመከላከልና ለማስቆም የአሰራር ማዕቀፎችን የመቅረፅ፣ የቅብብሎሽ ስርዓት የመዘርጋት፣ የአስፈፃሚ አካላትን አቅም የመገንባት፣ በተቋማት መካከል ቅንጅትን የመፍጠር እንዲሁም አገልግሎት አሰጣጡን የማሻሻል ስራ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።ሚኒስቴሩ ፍልሰትን ለመከላከል ከሚያካሂደው የግንዛቤና ንቅናቄ ባሻገር ለተመላሽ ዜጎች ጊዜያዊ ማረፊያ፣ የህክምና፣ የስነልቦና ምክር እንዲሁም የክህሎት ስልጠናና ሌሎችም አገልግሎቶች እንዲያገኙ የማስተባበር ስራ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

‎‎የመድረኩ ዓላማ ህጻናትን መደበኛ ካልሆነ ፍልሰት ለመጠበቅ እንዲሁም ተመላሽ ህጻናትን ከቤተሰባቸውና ከማህበረሰቡ ጋር መልሶ ለማዋሃድና ለማቀላቀል እንዲያስችል በተዘጋጀው ረቂቅ የአገልግሎት አሰጣጥ መስፈርት ላይ ለመወያየትና ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ እንደሆነ ገልጸዋል። ‎ድንበር ዘለል ትብብርንና ቀጣናዊ አጋርነትን ይበልጥ ለማጠናከር፣ የፍልሰት ተጎጂ ህፃናትን ጉዳይ አያያዝ እና የተመላሽ ህፃናትን መብት ለማስጠበቅ የሚያስችል ጠንካራ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ለመዘርጋት እና የሚከናወኑ ተግባራትም ስኬታማ ለማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ተገቢውን ትብብርና እገዛ ያደርጋል ብለዋል። በምክክር መድረኩ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የአለም አቀፍ ተቋማት የሆኑት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዩች እንዲሁም የምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ሀገራት (ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ ተወካዮች) እየተሳተፉ ይገኛል።
‎

Please follow and like us: