Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ለሴቶችና ለታዳጊ ሴት ልጆች የፍትህ ተደራሽነትን የሚገቱ መዋቅራዊ እንቅፋቶች እንዲወገዱ ጥሪ ቀረበ
ይህ ጥሪ የቀረበው በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) አዳራሽ እየተካሄደ ባለው በኢትዮጵያ ለሴቶችና ታዳጊ ሴት ልጆች የፍትህ ተደራሽነትን የሚገቱ መዋቅራዊ እንቅፋቶችን ለመፍታት በተዘጋጀ ከፍተኛ የፖሊሲ ውይይት መድረክ ላይ ነው።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደገለፁት ኢትዮጵያ የቤተሰብ፣ የወንጀል፣ የሰራተኛ፣ የመሬት እና የምርጫ ህጎችን በማሻሻል ረገድ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበች ቢሆንም፣ አሁንም በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሴቶች በህግ የተረጋገጡ መብቶች በተግባር ከመተርጎም አኳያ ሰፊ ክፍተት እንዳለ ጠቁመዋል ። በተለይም በወረቀት ላይ የሰፈሩትን ወደ ተግባር በመቀየር በሴቶች ህይወት ላይ ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት በጋራ የመስሪያ ጊዜ መሆኑን አሳስበው ለሴቶችና ለታዳጊ ሴት ልጆች የፍትህ ተደራሽነትን የሚገቱ መዋቅራዊ እንቅፋቶች እንዲወገዱ ጥሪ አቅርበዋል። ባለፉት አምስት ዓመታት መንግስት በርካታ ህጎችንና ፖሊሲዎችን ከስርዐተ ፆታ እይታ አንፃር የገመገመ ሲሆን፣ አዲስ የጾታ እኩልነትና የሴቶችን አቅም ማጎልበት ፖሊሲ በማርቀቅ ለመጨረሻ ውሳኔ መቅረቡን አስታውቀዋል ።
ከዚህ በተጨማሪም የጾታ ጥቃት ፈጻሚዎች መመዝገቢያ መዝገብ መተግበሩን፣ ፣ ነጻ የህግ ድጋፍ አገልግሎት መስፋፋቱን እና የተቀናጀ የህክምናና የህግ ድጋፍ የሚሰጡ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች ተደራሽነት መጨመሩን ገልጸዋል::ሚኒስቴሩ የሴቶችን መብት በግጭት ወቅት ለመጠበቅና በሰላም ግንባታ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ያለመውን ሀገራዊ የሴቶች፣ ሰላምና ደህንነት የድርጊት መርሃ ግብር እያጠናቀቀ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል ። በተጨማሪም የፍትህ ተደራሽነት ከሴቶች ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ጋር በቀጥታ የተቆራኘ መሆኑንም የገለፁ ሲሆን ሴቶች በመሬት፣ በንብረት፣ በፋይናንስና በስራ እድሎች ላይ እኩል ተጠቃሚ ካልሆኑ ፍትህ ሊረጋገጥ እንደማይችል አስገንዝበዋል ።
በመሆኑም የሴቶችን የኢኮኖሚ ጥንካሬ ማረጋገጥ ለሀገር እድገት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፣ የጾታ እኩልነትን የማረጋገጥ ስራ የአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆን የመላው መንግስትና የህብረተሰቡ የጋራ ኃላፊነት መሆን እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል ። መድረኩ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ፣በፍትህ ሚኒስቴር እና በተባበሩት መንግስታት የስርዐተ ፆታ ድርጅት (un_ women)በጋራ የተዘጋጀ ሲሆን ይህ መድረክ ዘንድሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ “50 ዓመታት የሴቶች ድምጽ ለእኩልነትና ለብልጽግና” በሚል መሪ ቃል የተከበረው ዓለም አቀፍ የሴቶች ወር ማጠቃለያ አካል መሆኑ ከመድረኩ ተጠቁሟል ።
