Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ሴቶች በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የመራጭነት ካርድ በመውሰድና ድምፃቸውን በመስጠት በሀገር ግንባታ ላይ የራሳቸውን አሻራ ሊያኖሩ ይገባል
ባለፉት የለውጥ ዓመታት መንግስት ለሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት መረጋገጥ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራና ተጨባጭ ውጤቶችም እየተመዘገበ መምጣቱ ይታመናል።

የሴቶችን የውሳኔ ሰጪነት ሚና ይበልጥ ማሳደግና በየዘርፉ ያላቸውንም ተጠቃሚነት በሚገባ ማረጋገጥ እንዲቻል ሴቶች በተለይ ለጠንካራ ሀገረ መንግስትና ለዳበረ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መሠረት በሆነው የምርጫ ሂደት ውስጥ በተሟላ መንገድ በንቃት መሳተፍ ይኖርባቸዋል። የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ምርጫው የሴቷን ህይወትም ሆነ የሀገሪቱን የወደፊት ዕጣ ፋንታ የመወሰን አቅም እንዳለው ከማስመዝገብ ባሻገር ሴቶች በመምረጥ፣ በመመረጥና በታዛቢነት ጭምር እንዲሳተፉ እንዲሁም ሁሉም የፓለቲካ ፓርቲዎች ከንግግር ባለፈ በተግባርም ጭምር ሴት እጩዎችን በማቅረብ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማስቻል በቅንጅት ሲሰራ ቆይቷል። በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ካርድ ያልወሰዱ እና እድሜያቸው ለምርጫ የደረሱ በገጠርም ሆነ በከተማ የሚገኙ መላው የሀገራችን ሴቶች በቀሪ ጊዜያት እንዲመዘገቡና የምርጫ ካርድ ባለቤት እንዲሆኑ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
በምርጫው እለትም፤ ሴቶች የራሳቸውን፣ የቤተሰባቸውንና የማህበረሰባቸውን ህይወት በተጨባጭ ይለውጣል፤ ሀገርንም ወደፊት ሊያራምድ ይችላል – በአጠቃላይም ለዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ሀገራዊ ዕድገት ይበጃል የሚሉትን የፖለቲካ ፓርቲ በነቂስ ወጥተው በመምረጥ በሀገር ግንባታ ላይ የራሳቸውን አሻራ እንዲያኖሩና የዜግነት ሃላፊነታቸውንም እንዲወጡ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ።
ክብርት ሒክማ ከይሬዲን
የሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ
