አለም አቀፍ የኢንዱስትሪ ሴቶች ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ተከበረ

‎አለም አቀፍ የኢንዱስትሪ ሴቶች ቀን በአለም ደረጃ እንዲከበር አምና በተወሰነው መሠረት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓሉ “Women’s Shaping the Future Industry” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

‎‎በዚሁ ወቅት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ ሴቶችበተለያዩ የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ ውስጥ በመሰማራት ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ግንባታ ሚናቸው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል። ሆኖም አሁንም ከብድር አቅርቦት፣ ከመስሪያ ቦታ፣ ዘላቂ የገበያ ትስስር ከመፍጠር፣ ከቴክኖሎጂ ተደራሽነትና ከክህሎት ጋር የተያያዙ ችግሮች እንደሚገጥሟቸው አንስተዋል።

‎ሴቶችን ከማብቃት ጎን ለጎን በሙሉ አቅማቸውና በእኩልነት በዘርፉ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲያደርጉ፣ በአምራችነት፣ በአመራርነትም ሆነ በፈጠራ ረገድ በአለም አቀፍ ደረጃ ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል። ‎የበዓሉ መከበር በኢንዱስትሪ ዘርፍ የሰማሩ ሴቶች የበለጠ ትኩረት እንዲያገኙ፣ የሚገጥሟቸው ችግሮች እንዲፈቱ እና በዘርፉ ራሳቸውንም ሆነ ሀገራቸውን  እንዲጠቅሙ ጉልህ አስተዋፅዖ ያበርክታል ሲሉ ተናግረዋል።

‎‎በተጨማሪም በዓሉ ለስርዓተ ፆታ አካታችነትና ለዘላቂ የኢንዱስትሪ ልማት ያለንን ቁርጠኛነት የሚያጠናክር መሆኑን ጠቅሰው የተባበሩት መንግስታት የኢንደስትሪ ልማት ድርጅት /UNIDO/ በዓሉ በኢትዮጵያ እንዲከበር ላበረከተው አስተዋፅዖ ምስጋና አቅርበዋል።

‎የዩኒዶ ተወካይና የሰብ ሪጅናል ጀነራል ዳይሬክተር ዶ/ር ስቴፈን ካርግቦ በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያ ሴቶች በቡና፣ በቆዳ፣ በማር አምራችና በሌሎችም አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችና የንግድ መስኮች ያላቸውን ተሳትፎና ጥረት አድንቀው፣ ዩኒዶ ሴቶችን አካታች ያደረገና ዘላቂ የኢንዱስትሪ ልማት እውን ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እንደሚሰራና ድጋፍም እንደሚያደርግ ገልፀዋል። መሪ ቃሉ ሴቶች ያላቸውን የፈጠራ ችሎታ፣ ፅናት እና ሁሉንም ያካተተ የአመራር ዘይቤና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ኢንዱስትሪዎችን እየቀየሩ እና የወደፊቱን አቅጣጫ እየወሰኑ መሆኑን ያመላክታል።

Please follow and like us: