በማህበራዊ ጥበቃ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከቱርክዬው ዲያኔት ዓለም አቀፍ ፋውንዴሽን እና በቱርክዬ ኢምባሲ የሃይማኖት ጉዳዮች ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል ፍሬያማ ውይይት መካሄዱን ክብርት ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ገለፁ

‎የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ በቱርክዬ የዲያኔት ዓለም አቀፍ ፋውንዴሽን ዳይሬክተር ቡራክ ኢንስ እና በቱርክዬ ኢምባሲ የሃይማኖት ጉዳዮች ዳይሬክተር ያሳር ቹሃዳርን ተቀብለው በጽህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል።

‎በውይይታቸውም፥ የቱርክ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት የቀደመና ታሪካዊ መሆኑን ክብርት ሁሪያ አንስተዋል። በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮችም ሀገራቱ በአጋርነት እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል። ‎ሁለቱም ተቋማት በኢትዮጵያ በተለይ በማህበራዊ ጥበቃ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በርካታ ስራዎችን እየሰሩ መሆኑን በመጥቀስ ምስጋና አቅርበዋል። የውይይቱ ዋና ዓላማም የማህበራዊ ጥበቃ ስራዎችን በተቀናጀና ዘላቂነት ባለው መልኩ እንዲሁም በዘመናዊ መንገድ አጠናክሮ ማስቀጠል የሚያስችሉ ተግባራትን በጋራ ለመስራት እንደሆነና ፍሬያማ ወይይት መደረጉንም ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ ሁሪያ አሊ አክለው ገልፀዋል።

‎የሁለቱም ተቋማት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን ህይወት በዘላቂነት ለመለወጥ የሚያግዙ ሰው ተኮር ፕሮግራሞችን ቀርፆ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን አድንቀዋል። ‎በቀጣይም መንግስት ቅድሚያ ሰጥቶ ለሚያከናውናቸው የማህበራዊ ጥበቃ ስራዎች ቱርክዬ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላትና በጋራ እንደምትሰራም አስታውቀዋል:: ‎ውይይቱን ተከትሎም ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ የትብብር መስኮችን የመለየት ስራ የተሰራ ሲሆን በቀጣይ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ወደ ተግባር ለመግባት የስራ ሃላፊዎቹ ተስማምተዋል።
‎

Please follow and like us: