‎በሳዑዲ ዓረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ 1 ሺህ 439 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ተመለሱ

በሳዑዲ ዓረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 1 ሺህ 439 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡
‎‎በሳምንቱ ውስጥ በተደረገ 7 ዙር በረራ የተመለሱት 1ሺህ 380 ወንዶች እና 57 ሴቶች እንዲሁም 2 ጨቅላ ህፃናት ሲሆን ከተመላሾች መካከል 49  እድሜያቸው ከአስራ ስምንት አመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ይገኙበታል። ‎መስከረም 5/ 2018 በተጀመረው ዜጎችን ወደ ሀገር ቤት የመመለስ ስራ እስካሁን ከ67 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገር መመለስ ተችሏል። ሚኒስቴሩ ለተመላሽ ዜጎች በአየር ማረፊያና በማቆያ ማዕከላት ተገቢውን ድጋፍ እና እንክብካቤ የማድረግ እና ከቤተሰብ ጋር የማቀላቀል ስራ ከሚመለከታቸው ባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በመተባበር በትኩረት እየሰራ ይገኛል። ‎በተጨማሪም መደበኛ ባልሆነ ፍልሰት ወደ ተለያዩ ሀገራት ሄደው የሚመለሱ የፍልሰት ተጎጂዎችን ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋም የሚያስችሉ ተግባራትን በትብብር እያከናወነ ይገኛል።
‎
‎በህገወጥ የሰዎች ዝውውር አስከፊነት ዙሪያ ህብረተሰቡን ለማስገንዘብ፣ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከልና ደህንነቱ የተጠበቀ ፍልሰትን ለማበረታታት ሚኒስቴሩ የጀመራቸውን ስራዎች ወደፊትም አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።

Please follow and like us: