በቅድመ ልጅነት ፕሮግራምና የህፃናት መንከባከቢያ ማዕከላት ማቋቋሚያ መስፈርትና አሰራር ዙርያ በሲዳማ ክልል የሚገኙ አስፈፃሚ አካላትን አቅም ለማጎልበት ያለመ ስልጠና ተሰጠ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከክልሉ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ እና ከሴቭ ዘ ችልድረን (Save the Childern) ጋር በመተባበር በቅድመ ልጅነት ፕሮግራምና ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጥቷል።

‎‎የሚኒስቴሩ የህጻናት መብትና ጥበቃ መሪ ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ዘቢደር ቦጋለ በመክፈቻ ንግግራቸው ከፅንስ ጀምሮ እስከ ስድስት አመት ያለው ጊዜ ከ90% በላይ የሰው ማንነት የሚቀረፅበት እድሜ ነው ብለዋል። ይሁንና ባለፉት ዘመናት በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ ላሉ ህፃናት ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶ ባለመስራቱ ዛሬ ላይ ወጣቶች እና ታዳጊዎች ስብዕና ላይ ክፍተቶች መኖሩን ገልፀዋል።  በቅድመ ልጅነት ፕሮግራምና የህፃናት የቀን ማቆያና መንከባከብያ ላይ የሚሰሩ ስራዎች በሙሉ ቤተሰብን፣ ቀጣይ ሀገርን የሚያሻግሩና የተሟላ ስብዕና ያለው  ትውልድን ለመፍጠር የሚረዳ መሆኑን ጠቁመዋል። ማዕከላቱ ህፃናት ደህንነቱ የተጠበቀ አካባቢ ላይ እንዲውሉና የአይምሮ እድገት እንዲኖራቸው የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

‎ማዕከላቱ ከሚኖራቸው ፋይዳ አኳያ ማህበረሰቡን በማስተባበር በሁሉም የሀገሪቷ ክፍሎች ማስፋፋትና ተደራሽ ማድረግ ይገባል ብለዋል።  ስልጠናው በቅድመ ልጅነት ፕሮግራምና የህፃናት መንከባከቢያ ማዕከላት ማቋቋሚያ መስፈርት እና አሰራር ዙርያ በክልሉ የሚገኙ አስፈፃሚ አካላትን አቅም በማጎልበት በእውቀት ላይ የተመሠረተ ውጤታማ ስራ  እንዲሰሩ ለማስቻል ያለመ እንደሆነ ገልፀዋል።

‎‎የክልሉ የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ም/ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ፍጹም በላይ በበኩላቸው፥ የህፃት የቀን ማቆያና መንከባከቢያ ማዕከላት ህፃናት ብቻ ሳይሆን የሚጠቀሙት እናቶችም ለስራቸው ትኩረት እንዲሰጡ በተረጋጋ መንፈስ በተሰማሩበት የሰራ መስክ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የሚያደርግ በመሆኑ ያገኙትን ግንዛቤ በስራ ላይ እንዲያውሉ አሳስበዋል።

በመድረኩ የህፃናት የቅድመ ልጅነት ዘመን ዕድገትና ትምህርት ፖሊሲ እና የማስፈፀሚያ ስትራቴጂ፣ የህፃናት መንከባከቢያና ማዕከላት ማቋቋሚያ መስፈርት እና አሰራርን ለመወሰን የወጣ መመሪያ 1084/2017 እንዲሁም በአዎንታዊ የህፃናት አስተዳደግ ዙሪያ እና የቀዳማይ ልጅነት እንክብካቤን መረዳትና የባለድርሻ አካላት ሚና ላይ ያተኮረ ሙያዊ ገለፃ ተደርጓል:: ሰልጣኞችም በተሰጣቸው ስልጠና ሰፊ ግንዛቤ እንደተፈጠረላቸው ገልፀው ቀጣይነት እንዲኖረው ጠይቀዋል። በመርሐ ግብሩ ከሀዋሳ ከተማ አስተዳደር፣ ከዞንና ከወረዳ የተውጣጡ የጤና ቢሮ፣ የትምህርት ቢሮ፣ የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ እንዲሁም የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

‎

Please follow and like us: