Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
በምርጫ ወቅት በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለመከላከል አዲስ አሠራር ጸደቀ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫ ወቅት በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አዲስ መደበኛ የአሠራር ሥርዓት አጸደቀ።
ጥቃቱን በጋራ ለመከላከል የትኞቹ ተቋማት ምን መሥራት እንዳለባቸው በግልጽ ባስቀመጠው አሠራር ቦርዱን ጨምሮ 10 የተለያዩ የመንግሥትና የሲቪል ማኅበራት ተቋማት ኃላፊነታቸውን በጋራ ለመወጣት ተስማምተው ፈርመዋል። በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የምርጫ ቦርድ፣ የፍትሕ ሚኒስቴር፣ የፌደራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን፣ እንዲሁም የተለያዩ የሲቪል ማኅበራትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት ተወካዮች ተገኝተዋል። የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፣ ይህ የአሠራር ሥርዓት በምርጫ ወቅት የሴቶችን ደኅንነትና እኩልነት ለመጠበቅ የተዘጋጀ የመጀመሪያውና ልዩ ሠነድ ነው።
ቦርዱ ከተመሠረተ ጀምሮ ለሥርዓተ-ፆታ እኩልነት ትኩረት በመስጠት የተለያዩ ፖሊሲዎችንና ሥልጠናዎችን ሲያዘጋጅ መቆየቱንም ገልጸዋል። ሰብሳቢዋ አክለውም፣ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ ፆታዊ ጥቃቶችን ማስቆም ወሳኝ መሆኑን ማስገንዘባቸውን የምርጫ ቦርድ መረጃ ያመላክታል።
ይህ አዲስ አሠራር ጥቃቶችን አስቀድሞ ለመከላከል፣ የደረሱ ጥቃቶችን በስምምነት ለመመዝገብ፣ ፈጣን ምላሽ ለመስጠትና የጥቃት ሰለባዎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ግልጽ መንገድ እንደሚያሳይ አብራርተዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።
