በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ላይ የሚሠጡ ምላሾች ልብ ጠጋኝ መሆን ይገባቸዋል -ክብርት ሂክማ ከይረዲን

ይህ የተገለፀው በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና በፍትህ ሚኒስቴር አስተባባሪነት ለሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀም ጥቃትን ለመከላከልና እና ምላሽ ለመስጠት በተቋቋመው ብሔራዊ አስተባባሪ አካል አደረጃጀትና አሰራር ወጥና በተናበበ መልኩ ለመተግበር በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ነው።

በዕለቱ የሚኒስቴር መ/ቤቱ የሴቶችና ህፃናት ዘርፍ ሚኒስቴር ድኤታ ክብርት ሂክማ ከይረዲን እንደገለፁት በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሱ ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እንዳይደርሱ እና መከላከል ላይ በይበልጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ጥቃት ከደረሰ በኃላም ከፍትህ አካላት የሚሠጡ ምላሾች ልብ ጠጋኝ መሆን እንደሚገባቸው ገልፀዋል። በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ለመከላከልና ከደረሰም በኃላ ምላሽ ለመስጠት ባለፉት የለውጥ አመታት ለውጦች መታየታቸዉን ገልፀው ነገርግን አሁንም ከችግሩ ጥልቀት አንፃር በቂ ባለመሆኑ አሠራሩን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ወጥነት ባለውመልኩ እንዲሠሩ አሳስበዋል። የተቋቋመው ብሔራዊ አስተባባሪ አካልም የጥምረቱ አባል በሆኑና ባለድርሻ አካሎችን በማስተባበር በሴቶችና በህፃናት ላይ የሚፈፀም ጥቃትን ወጥ በሆነና በተቀናጀ መልኩ ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት ያግዛል ብለዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ከጊዜ ወደ ጊዜ ባህሪያቸው አየተወሳሰቡና እየረቀቁ በመምጣታቸው የፍትህ ስርዐቱን በማዘመንና ዘመኑን የዋጀ በማድረግ ምላሽ ለመስጠት በመሰራት ላይ እንዳለ ገልፀዋል። መሠል ስራዎችን በጣምራ መስራቱም ዜጎች የተሟላ ፍትህ እንዲያገኙ ከማስቻል ባለፈ ኃላፊነትን በጋራ ለመወጣትና የተጠያቂነት ስርዐትን ለማስፈን እንደሚረዳ ጠቁመዋል። የብሔራዊ አስተባባሪ አካሉ በተቀናጀና ሁሉን አቀፍ በሆነ መንገድ ጥቃቶችን ለመከላከልና የሕፃናትን ፍትሕ ለማረጋገጥ ያስችለው ዘንድ በድጋሚ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የአሠራር ስርዐቱን በማፅደቅ ወደ ስራ መግባቱ ይታወሳል።

Please follow and like us: