Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን በመከላከል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሚዲያ አካላት እውቅና ተሰጠ
በኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በአለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (IOM) ትብብር የተዘጋጀው የሚዲያ ተቋማትና ባለሙያዎች የዕውቅና አሰጣጥ ፕሮግራም በይፋ ተካሂዷል ።
በሚኒስቴሩ የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከልና የየተመላሾች ክትትልና ቁጥጥር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ ተግይበሉ ስደትና ከስደት ተመላሾች መንግስት ይህንን ውስብስብ ችግር ለመፍታትና ዜጎችን ከህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ለመጠበቅ አዋጅ ቁጥር 1178/2012 ማውጣቱንና ብሔራዊ ምክር ቤት አቋቁሞ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል:: በዚህም መሰረት ባለፉት አራት ዓመታት ብቻ ከተለያዩ የአፍሪካ፣ የመካከለኛው ምስራቅና የምዕራብ ሀገራት (የአሜሪካንና ማይናማርን ጨምሮ) ከ500 ሺህ በላይ ለችግር የተጋለጡ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን ወደ ሀገራቸው በመመለስ፣ የስነ-ልቦና ድጋፍና መልሶ የማቋቋም ስራዎች መከናወናቸው ጠቅሰዋል ።
ይሁን እንጂ የህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ስልትና መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት አሁንም በስፋት እየቀጠለ በመሆኑ ፣ የማህበረሰቡን ግንዛቤ በማሳደግና የአመለካከት ለውጥ በማምጣት ረገድ የሚዲያ አካላት ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል። ይህ የዕውቅና ፕሮግራም የተዘጋጀውም፣ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ከመከላከል አንጻር በህትመት፣ በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ እና በማህበራዊ ሚዲያ ጥራትና ስነ-ምግባር ያለው ዘገባ በማቅረብ ማህበረሰቡን ያነቁና ውጤታማ የሆኑ የሚዲያ ተቋማትና ባለሙያዎችን በማበረታታት እውቅና ሰጥቷል።
Please follow and like us:
