Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ለጥቃት ተጋላጭና ተጎጂ የሆኑ ሕጻናትን ለመንከባከብ እና ወደነበሩበት ሁለንተናዊ ደህንነት ለመመለስ በሚከናወኑ ተግባራት ዙሪያ የህጻናት ባለሙያዎችን፣ የፖሊስ አካላትንና የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎችን አቅም ለማጎልበት ያለመ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል
የሚኒስቴሩ የህፃናት መብት ጥበቃ መሪ ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ዘቢደር ቦጋለ ባስተላለፉት መልዕክት፤ሕፃናት በተዛቡ አመለካካቶች፣ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ክስተቶች ምክንያት ለተለያዩ ጥቃቶች ተጋላጭ የሚሆኑባቸው እድሎች ሰፊ እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡
በተለይም በህፃናት ላይ የሚፈፀም አካላዊ፣ ወሲባዊ፣ ስነ-ልቦናዊና ስሜታዊ ጥቃት በሕጻናት የአሁንና የወደፊት ሕይወት ላይ ጥልቅ የሆነ ሥነ-ልቦናዊ ጠባሳ፣ የማህበራዊ መገለል እና የጤና እክሎችን ከማስከተሉም በላይ ውድ ህይወትን ሊያሳጣ እንደሚችል ተናግረዋል። ሕጻናት በአካል፣ በሥነ-ልቦና እና በማህበራዊ ተጠቃሚነት ረገድ ጤናማ ሆነው እንዲያድጉ ልዩ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል ያሉት ወ/ሮ ዘቢደር የህጻናትን ጥበቃ ለማጎልበት የሚያስችሉ የህግ፣ የፖሊሲ ማእቀፎችን ማዘጋጀትና ተግባራዊ ማድረግ እና የአሰራር ስርዓቶችን ከመዘርጋት ባሻገር ህብረተሰቡን ያሳተፈ የመከላከልና ምላሽ የመስጠት ስራዎችን መስራት ይገባል ብለዋል።

በተጨማሪም የባለሙያዎችን /front line workers/ እውቀት በማሳደግ የህጻናትን ጥቃትና ተጋላጭነት መቀነስ፤ ለጥቃት ሲጋለጡም ፈጣን ምላሽ የተናበበና የቅብብሎሽ አገልግሎት የሚያገኙበትን ተቋማዊ አሰራሮች ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

ከጥቃት የተረፉትን ሕጻናት ለመንከባከብ፣ ምላሽ ለማመቻቸት እና ወደነበሩበት ሁለንተናዊ ደህንነት ለመመለስ የሚከናወኑ ተግባራት ልዩ ጥንቃቄን፣ ሙያዊ ክህሎትን እና ርህራሄን ይጠይቃል ብለዋል።
በዘርፉ የሚሰሩ አገልግሎት ሰጪዎችንም ከስራው ጋር ተያይዞ ከገቡበት የስነልቦና ጫና እንዲወጡ እና የህጻናትን ሁለንተናዊ ደህንነት ለማስጠበቅ የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ስልጠናው መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡ በስልጠናው ከሁሉም ክልልና ከተማ እስተዳደር የተውጣጡ የህጻናት ባለሙያዎች፣ የፖሊስ አካላት፣ የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት እየተሳተፉ ይገኛል።
