Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም የዜጎችን ሕይወት ከተረጂነት ወደ አምራችነት እያሸጋገረ መሆኑ ተገለጸ
በገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም (PSNP) የአምስተኛው ምዕራፍ ማጠቃለያና የዕውቀት ሽግግር መድረክ ላይ እንደተገለፀው የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና የግብርና ሚኒስቴር በገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም የዜጎችን ህይወት ከተረጂነት ወደ አምራችነት እያሸጋገረ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደገለፁት ፕሮግራሙ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ የ8 ሚሊዮን ዜጎችን ሕይወት የቀየረና በየአምስት ዓመቱ 50 በመቶ የሚሆኑ ተጠቃሚዎች ከተረጂነት ወጥተው ወደ አምራችነትና ሥራ ፈጣሪነት እንዲሸጋገሩ ያስቻለ ጠንካራ የማኅበራዊ ጥበቃ መሠረት መሆኑን ጠቅሰዋል። ሚኒስቴሩ በተለይም የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አዲስ ብሔራዊ የሴቶች አቅምና የሥርዓተ ጾታ እኩልነት ፖሊሲ በሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ ማድረጉንና ይህም በስድስተኛው ምዕራፍ የሴፍቲኔት ፕሮግራም ውስጥ የሴቶችን ተጠቃሚነት በላቀ ደረጃ ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ሚኒስቴሩ በ2025 ዓ.ም. ብሔራዊ የማኅበራዊ ጥበቃ ፖሊሲን በመከለስ፣ ዘመናዊና የተቀናጀ የዲጂታል ማኅበራዊ መዝገብ (National Social Registry) በመዘርጋት እንዲሁም የቅድመ ልጅነት ፕሮገራም (ECD) ማዕከላትን በማስፋፋት እናቶች በሥራ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ እያደረገ መሆኑን አመላክተዋል። በዚሁ መድረክ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትር ድኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤልያስ በበኩላቸው ፕሮግራሙ ወደ ዘላቂ ልማት የሚያሸጋግር አስተማማኝ መደላድል እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል። ፕሮግራሙ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥና ከቀጥታ የገንዘብ ድጋፎች ባሻገር በድህነት ቅነሳ፣ በአፈርና ደን ጥበቃ ላይ በትኩረት የሚሠራ በመሆኑ ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ለሥነ-ምህዳር መታደስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልፀዋል።

የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎችም ከዕለት ድጋፍ በላይ ዘላቂና አስተማማኝ በሆነ መልኩ ከተረጂነትና ከጠባቂነት ተላቀው፣ በምርትና ምርታማነት ሥራዎች ላይ ተሰማርተው የራሳቸውንና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እንዲደግፉ ማስቻል መሆኑን ጠቅሰዋል። ሁለቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ማኅበራዊ ጥበቃንና የግብርና ልማትን በማስተሳሰር፣ ተጋላጭ ዜጎች በተለይም ሴቶችና ሕፃናት የልማቱ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ ለማረጋገጥ በቅንጅት እየሠሩ መሆኑ በመድረኩ ላይ አረጋግጠዋል ።
በዕለቱም ከሴፍትኔት ቀጥታ ድጋፍ በመውጣት ምርታማ የሆኑ ተጠቃሚዎች ስራዎቻቸውን አስጎብኝተዋል።
