የማኅበራዊ ጥበቃ ስርዐት በዜጎችና በሀገር ላይ የሚሠራ ሀገራዊ የሰው ሀብት ልማት አካል መሆኑ ተገለፀ።

ይህ የተገለፀው የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስተሮችን አካቶ በመካሄድ ላይ ባለው የገጠር ልማታዊ  ሴፍቲኔት ፕሮግራም የእውቀት ሽግግር መድረክ ላይ በሰው ሀብት ልማትን ለዘላቂ የማኅበረሰብ አቅም ግንባታ ዙሪያ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።

የሚኒስቴሩ የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስቴር ድኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ በውይይቱ ወቅት እንደገለፁት ማኅበራዊ ጥበቃን እንደ እርዳታና ችሮታ የሚታይ ሳይሆን የማኅበራዊ ጥበቃ ስርዐት በዜጎችና በሀገር ላይ የሚሠራ ሀገራዊ የሰው ሀብት ልማት  አካል መሆኑ ገልፀዋል። ቀደም ባሉት ዓመታት ትልቁ ፈተና ተቋማት የሰው ሀብትን በቅንጅት ከመጠቀም ይልቅ በተናጠልና በተጓዳኝ መጓዛቸው እንደነበር ጠቁመዋል።

በመሆኑም አዲሱ ስድስተኛው ምዕራፍ የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም (PSNP 6) መሠረታዊ የሆነ የአስተሳሰብና የስልት ለውጥ ይዞ የመጣ መሆኑንና ትኩረቱን ከተቋማዊ ግብ ወደ ቤተሰብ ማዕከልነት ያዞረ መሆኑን አብራርተዋል።  ፕሮግራሙ ዜጎችን ድንገተኛ ፈተናዎችን እንዲቋቋሙ ከመደገፍ ባለፈ፤ የሕፃናት የአእምሮ ዕድገትና የተሟላ ጤና የሚወሰንበትን የመጀመሪያዎቹን አንድ ሺህ ቀናት  እንደ ትልቅ ሀገራዊ የኢኮኖሚ አጀንዳ ወስዶ መሥራት እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።

በዚህ የለውጥ ጉዞ ውስጥ የዲጂታል አካታችነትን ማረጋገጥ ዋነኛው ምሰሶ መሆኑን ገልፀው በአሁኑ ወቅት ከ1 ሚሊዮን በላይ የሴፍቲኔት ተጠቃሚ አባወራዎች ከማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ጋር መተሳሰራቸውንና በማኅበራዊ መዝገብ ሥርዓት ውስጥ እንዲካተቱ እየተደረገ መሆኑን ይፋ አድርገዋል። የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በተፈጥሮ ሀብት ብቻ ሳይሆን በሕዝቦቿ የእውቀትና የክህሎት አቅም ላይ የሚመሠረት በመሆኑ፤ የሰው ሀብት ልማት የአንድ ተቋም ሳይሆን የሁሉም አካላት የጋራ አገራዊ ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ከአፍሪካ የቅድመ-መደበኛ ሕፃናት ዕድገት ማዕከል፣ ከጤና ሚኒስቴር እና ከዩኒሴፍ (UNICEF) የተወከሉ የፓናል ተወያዮች በመድረኩ ላይ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ተወያዮቹ በተለይ የሕፃናትን የአእምሮና የአካል ብቃት ለማሳደግ የሚረዱ የቅድመ-መደበኛ የትምህርትና የእንክብካቤ ፕሮግራሞችን ማስፋፋት፣ የተቀናጀ የጤና እና የስነ-ምግብ አገልግሎቶችን ማቅረብ፣ እንዲሁም የሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጠቃሚዎችን የንጹህ መጠጥ ውሃና የንፅህና አጠባበቅ (WASH) ተጠቃሚ ማድረግ የሰው ሀብት ልማት ውጤታማነቱን ዘላቂ ለማድረግ ወሳኝ መሆናቸውን በጋራ አረጋግጠዋል።

Please follow and like us: