ዓለም አቀፍ የአረጋውያን ጥቃት ግንዛቤ የመፍጠር ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ ተከበረ

በዓለም ለ20ኛ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ11ኛ ጊዜ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የአረጋውያን ጥቃት ግንዛቤ የመፍጠር ቀን “በአረጋውያን ላይ ስለሚደርሱ ጥቃቶች ግንዛቤ እንፍጠር፤ ችግሩንም በትብብር እንከላከል!!” በሚል መሪ ቃል በሀርመኒ ሆቴል ተከብሯል።

በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ንግግር  በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአረጋውያንና ቤተሰብ ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ተስፋዬ ሮበሌ፣ አረጋውያን የሀገርና የትውልድ ባለውለታ ቢሆኑም፣ በአሁኑ ወቅት ከከተሞች መስፋፋትና ከእሴቶች መሸርሸር ጋር ተያይዞ ለኢኮኖሚያዊ፣ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጥቃቶች እየተጋለጡ መሆኑን ገልጸዋል። ይህን ችግር ለመቅረፍ መንግስት የአፍሪካ የአረጋውያን መብቶች ፕሮቶኮልን በአዋጅ ማጽደቁንና ጉዳዩ በሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶች ተካትቶ እንዲሰራ መደንገጉን አቶ ተስፋዬ አስታውሰዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም የአረጋውያንን መብት ለማስከበርና ከጥቃት ለመጠበቅ የፖሊሲ ማዕቀፎችን ከማዘጋጀት ባለፈ የአድቮኬሲና የንቅናቄ ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የአረጋውያንን ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ በቅንጅትና በትብብር እንዲረባረቡ መሪ ስራ አስፈፃሚው ሀገራዊ ጥሪ አቅርበዋል። በተጨማሪም ከኢትዮጵያ አረጋዉያን ጡረተኞች ብሔራዊ ማህበር፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እና ሄልፕ ኤጅ ኢትዮጵያ የተገኙ ሃላፊዎች መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን በመልዕክታቸው እንደገለፁት  ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚ/ር፣ ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እና ከኢተዮጵያ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር የአረጋዊያንን መብት ጥሰት ለመከላከል በተሰራዉ ስራ አመርቂ ዉጤት መገኘቱን ጠቂሰዉ ለወደፊትም ተጠነክሮ መቀጠል እንዳለበት ገለፀዋል፡፡

Please follow and like us: