‎ከ52 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆኑ የቢሮ ቁሳቁሶች (Furniture) እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (IT) መሣሪያዎች ለፌዴራልና ለ5 ክልል የስርዓተ ፆታ መዋቅሮች ድጋፍ ተደረገ

በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ለሚተገበረው “የሥርዓተ-ፆታ መዋቅር ፕሮጀክት” (Gender Machinery Project) ማስፈፀሚያ የሚውል ከ52 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የቢሮ ቁሳቁሶች(Furniture) እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (IT) መሣሪያዎች ድጋፍ ተደርጓል።

‎በቁሳቁስ ድጋፍ ርክክብ ሥነ-ሥርዓት ላይ ክብርት ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ፥ የድጋፉ ዋና ዓላማ የሥርዓተ-ፆታ እኩልነትን ለማስፈንና የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚሰሩ ተቋማትን አቅም በማጎልበት የውሳኔ ሰጪ እና አስፈጻሚ አካላት ሥራቸውን በብቃትና በዘመናዊ መልክ ማከናወን እንዲችሉ ለማስቻል እንደሆነ ገልፀዋል። ‎ፕሮጀክቱ ሚኒስቴሩ ከዩ ኤን ውመን (UNWOMEN) እና ከዩ ኤን ኤፍ ፒ (UNFPA) ጋር በመተባበር እየተገበረ የሚገኝ ሲሆን በዋነኝነትም የአካቶ ትግበራን፣ የስርዓተ ፆታ መረጃ አያያዝና አጠቃቀምን እንዲሁም የአስፈፃሚ ተቋማትንና ባለሙያዎችን አቅም ማሳደግ ላይ ያተኮሩ ተግባራት እንደሚተገበሩ ተናግረዋል። ድጋፉ ‎በቁሳቁስና የቴክኖሎጂ እጥረት ምከንያት በሴቶችና ህፃናት ዙሪያ ሊሰሩ የታቀዱ ተግባራትን በማሳካት ረገድ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በማቃለል ፕሮጀክቱን ውጤታማ ለማድረግ የበኩሉን እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

‎‎ክብርት ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ከአውሮጳ ህብረት (European Union) እና ከስፓኒሽ ኮርፖሬሽን ኤጀንሲ(Spanish Corporation Agency) በተገኘ የገንዘብ ድጋፉ ግምቱ ከ52 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ኮምፕዩተር፣ ላፕቶፕ፣ ስካነር እና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስና የቢሮ መገልገያ ቁሳቁሶችን ለሚመለከታቸው የክልልና የፌዴራል የስራ ኃላፊዎች አስረክበዋል። ድጋፉ የተደረገው ለጋምቤላ፣ አማራ፣ አፋር፣ ሱማሌና ለትግራይ ክልል ሴክተር ቢሮዎች ሲሆን የስራ ሃላፊዎቹ በተደረገው ድጋፍ መደሰታቸውን ገልፀዋል።

Please follow and like us: