Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
በኢትዮጵያ የወር አበባ ንፅህና አጠባበቅ ሥርዓትን ለማጠናከር የፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ (AFD) ድጋፍ እንዲሚያደርግ አስታወቀ
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ (AFD) የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የአፍሪካ ህብረት (AU) ተወካይ ሉዊስ-አንቶዋን ሱሼ እና የውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅና የጾታ እኩልነት አስተባባሪ ማርጎ ሺና እና ልዑካቸው ጋር በሴቶች የወር አበባ ንፅህና አጠባበቅ ስርዓት ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።
በመድረኩ የወር አበባ ንፅህና አጠባበቅ ሥርዓትን ለማጠናከር የተቋቋመው (የMAP-PPD) ብሔራዊ ፎረም የአሠራር እና የቅንጅት ተግዳሮቶችን ከመፍታት አኳያ እስካሁን የተመዘገቡ ዋና ዋና ስኬቶችና የፖሊሲ ውጤቶች የተዳሰሱ ሲሆን በቀጣይም ፕሮጀክቱን ይበልጥ ለማሳደግ (Scale up) በትብብር መሥራት አስፈላጊነት ላይ በሰፊው መክረዋል። በተጨማሪም የስራ ሃላፊዎቹ በግሉ ዘርፍ በኩል ተጨባጭ ውጤት ማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በጥልቀት የተወያዩ ሲሆን፥ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ምርታቸውን በጥራትና በስፋት እንዲያቀርቡ በፕሮጀክቱ በኩል ድጋፍ እንዲጠናከር መግባባት ተደርሷል።
ክብርት ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በዚሁ ጊዜ፥ ሴት ተማሪዎች የንፅህና መጠበቂያ ምርቶችን እንዲያገኙ ለማድረግ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሳኒተሪ ፓድ ማከፋፈያ ማሽኖችን (Sanitary Pad Dispensing Machines) ለመግጠም እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልፀዋል። የፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ (AFD) ወደፊትም ማሽኖቹን ተደራሽ በማድረግ፣ ጥራታቸውን የጠበቁና ዋጋቸው ተመጣጣኝ የሆኑ የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን በማቅረብ እንዲሁም ሚኒስቴሩ የጀመረውን ተነሳሽነት በገንዘብና በቴክኒክ እንዲደግፍ ክብርት ሚኒስትሯ ጥሪ አቅርበዋል። የAFD ዳይሬክተር ሉዊስ-አንቶዋን ሱሼ በበኩላቸው፥ የፕሮጀክቱን ስኬታማነትና የፖሊሲ ውጤቶች በማድነቅ ፕሮጀክቱ በዘላቂነት እንዲቀጥል እና አዲስ የድጋፍ ምዕራፍ እንዲጀመር (Project Renewal) ኤጀንሲው አጋርነቱን እንደሚያጠናክር ገልፀዋል።
