Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ሚኒስቴሩ እና አለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን በመከላከልና የፍልሰት ተመላሾችን መልሶ በማቋቋም ላይ ያላቸውን ስትራቴጂክ አጋርነት ለማጠናከር ተስማሙ
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ የአይ ኦ ኤም (IOM) የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጠና ምክትል ዳይሬክተር ሚስ ኒሃን ኤርዶጋን እና በዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቢባቱ ዋኔ-ፎልን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
የስራ ሃላፊዎቹ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከል በሚስያችሉ ስትራቴጂክ ጉዳዮች፣ የፍልሰት ተመላሾች የቅብብሎሽ የአሰራር ስርዓቱም ከፌዴራል ጀምሮ በክልል፣ በዞን፣ በወረዳና በቀበሌ ደረጃ ውጤታማ በሆነ መልኩ ተግባራዊ ስለሚሆንበት፣ ከፍልሰት ተመላሾ በሀገራቸው ሰርተው እንዲለወጡና ለዳግም ስደት እንዳይጋለጡ ዘላቂ የኢኮኖሚ ድጋፍ ስለሚያገኙበት ሁኔታ በሰፊው ተወያይተዋል። በተጨማሪም የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት የገነባቸውንና የሚያስተዳድራቸውን ጊዜያዊ መጠለያዎች በዘላቂነት አገልግሎት ስለሚሰጡበትና አስተዳደራቸውን በተመለከተ ስለተዘጋጀው እቅድ እንዲሁም በፍልሰት ተመላሾችና መልሶ ማቋቋም ዙሪያ የተጠናከረ መረጃ ስርዓት ለመዘርጋት እንዲያስችል በለማው ዳታ ቤዝ ላይ በጥልቀት መክረዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ገለጻ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት ጋር የአምስት አመት የጋራ ስትራቴጂክ እቅድ በማዘጋጀት ወደ ስራ መገባቱንና ለእቅዱን ስኬታማነትም ድርጅቱ አበረታች ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን በመጥቀስ ምስጋና አቅርበዋል። በቀጣይም በተጠቀሱት የትብብር መስኮች ድርጅቱ ስትራቴጂክ አጋርነቱን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል። የአይ ኦ ኤም (IOM) የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጠና ምክትል ዳይሬክተር ሚስ ኒሃን ኤርዶጋን በበኩላቸው፥ በሀገሪቱ እየታየ ያለውን ፈጣን እድገት አድንቀዋል። በማህበራዊ ጥበቃ፣ ሴቶችን በማብቃትና በሌሎችም ዘርፎች መንግስት አበረታች እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አመላክተዋል። ፍልሰትን በተመለከተም ቅድሚያ በሚሰጣቸው ስትራቴጂክ ጉዳዮች ላይ የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት በቅንጅት እንደሚሰራ እረጋግጠዋል።
