Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ሚኒስቴሩ በ5 ክልሎች 30 የቅድመ ልጅነት ዘመን ዕድገት ማዕከላትን ለአገልግሎት ክፍት አደረገ
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት እንዲሁም የክልልና የወረዳ መዋቅሮችን በማስተባበር በተመረጡ 5 ክልሎች የገነባቸውን 30 የቅድመ ልጅነት ዘመን ዕድገት ክብካቤ ማዕከላት በይፋ ለአገልግሎት ክፍት በማድረግ ለተጠቃሚዎች አስተላልፏል።
በዕለቱ የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ የሆኑት ክብርት ሁሪያ አሊ እንደገለፁት በገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም መንግስት በተለያዩ ምክንያቶች ለማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስችሉ የተለያዩ የማህበራዊ ጥበቃ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ እንደሚገኝና በውጤቱም ተጨባጭ ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑን አስገንዝበዋል። እናቶችን ከስራ ገበታ በማስቀረትና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎን በመግታት ሀገር ልታገኝ የምትችለውን ጥቅም በማስቀረት ሚናቸውን በቤት ውስጥ ብቻ ተወስኖ እንዲቀር ከሚያስገድዱ ተግዳሮቶች መካከል በአቅራቢያቸው የህፃናት ማቆያና መንከባከቢያ ማዕከል አለመኖሩ ዋነኛው ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ሲባልም የቅድመ ልጅነት ዘመን ዕድገት ማዕከላትን መገንባትና ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ እንደሚገባ አስፈላጊነቱ ታምኖበት የፕሮግራሙ አካል እንዲሆን ተደርጓል።
ይህም የአካባቢ ጥበቃ ልማት ስራዎች ላይ በመሳተፍ ላይ ያሉ እናቶች ስራቸውን በሙሉ ትኩረትና ጉልበት እንዲያከናውኑ የማዕከላቱ ግንባታ እንደሚያግዝ ገልፀዋል። ማዕከላቱ በመማሪያ አካባቢዎች መገንባታቸው ህፃናት ጤናማና ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሁም በስነ ልቦናና አካላዊ ብቃት የበቁ ሆነው እንዲያድጉ ያግዛል ብለዋል። ማዕከላቱ በተቀመጠላቸው ስታንዳርድና የአሰራር መመሪያ መሰረት ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ፣ ተባብሮ መስራትና ማዕከላቱን በአግባቡ ተንከባክቦ መያዝ የሁሉም ሀላፊነት እንዲሆን ሚኒስትር ዴኤታዋ አሳስበዋል። በሙከራ ደረጃ የተጀመረው ይህ ስራ ቀጣይነት የሚኖረው ሲሆን ዛሬ በሲዳማ ክልል በሃዌላ ቱላ ክፍለ ከተማ በይፋ የተከፈተውን ጨምሮ ባሉ ሌሎች ማዕከላት የሚገኘው መልካም ተሞክሮ ለቀጣዩ ማስፋፊያ በጎ ጅምር እንደሚሆን ገልፀዋል ።
የሲዳማ ክልል ሴቶች ወጣቶች ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ም/ል ኃላፊና የማሀበራዊ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ባንታየሁ ቀጸላ በበኩላቸው በህጻናት አዕምሮ ላይ የምንሰራው ሥራ አና የምናደርገው አንክብካቤ ለወደፊት ተመራማሪና ችግር ፈቺ ትውልድ በመፍጠር ድህነትን ለመቀነስና እድገት ለማምጣት የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል ። ዛሬ ይፋ የተደረጉት ማዕከላት በዘላቂነት አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ክልሎች አስፈላጊውን ተጨማሪ ግብዓት በማሟላት፣ ተገቢውን ክትትልና ጥበቃ በማድረግ የማዕከላቱን ጠቀሜታ ይበልጥ ትርጉም ያለው እንዲያደርጉትም አሳስበዋል።
