Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
በኢትዮጵያ በሴቶች የሚመሩ አደረጃጀቶችን ለመደገፍና የሴቶችን ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ስትራቴጂካዊ የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ
በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በኬር ኢትዮጵያ መካከል በካናዳ መንግሥት የሚደገፈውን በሴቶች የሚመሩ አደረጃጀቶችን ለመደገፍና የሴቶችን ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረው ይህ ፕሮጀክት ይህንን በግንባር ቀደምትነት የሚመሩ ስድስት ሀገር በቀል ድርጅቶች ይመሩታል፡፡
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በስምምነቱ ወቅት እንደተናገሩት ይህ አጋርነት ማኅበራዊ አካታችነትን ለማጠናከር እና ሀገራዊ ፖሊሲዎችን በተግባር ለመተርጎም የሚያስችል ስትራቴጂካዊ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።
ስምምነቱ ወጣቶችን፣ ሴቶችን እና አካል ጉዳተኞችን የሚያካትቱ ድርጅቶች በልማቱ ላይ ተመልካች ብቻ ሳይሆኑ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የሚወስኑ ባለቤቶች እንዲሆኑ እንደሚያስችላቸው አስገንዝበው የካናዳ መንግሥት በካናዳ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች (Global Affairs Canada) በኩል ላደረገው የገንዘብ ድጋፍ አመስግነዋል፡፡
በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ኒኮላስ ሲማርድ፣ ካናዳ ይህንን ፕሮጀክት ለመደገፍ በመቻሏ ታላቅ ኩራት እንደሚሰማት ገልጸው ይህም ካናዳ በኢትዮጵያ ተቋማት፣ በሲቪል ማኅበረሰብ እና በኢትዮጵያውያን ሴቶች የአመራር ብቃት ላይ ያላትን የጠነከረ እምነት የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል። ሴቶች የአመራር ሚና እና በኢኮኖሚው ላይ እኩል ተሳታፊ ሲሆኑ ምጣኔ ሀብቱ ይበልጥ ጠንካራ እንደሚሆን የገለጹት አምባሳደሩ ይህንን የአምስት ዓመት ፕሮጀክት ጠቅሰው፣ ይህም በሂደት ከ100 በላይ የሴቶች መብት ተሟጋች ድርጅቶችን እንደሚያጠናክር አብራርተዋል።
የኬር ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ማህተመ ምክሬ ( ዶ/ር) በበኩላቸው ስምምነቱ በመንግሥት፣ በሲቪል ማኅበራት እና በልማት አጋሮች መካከል ያለውን የጋራ ትብብር ይበልጥ እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱን ከሚመሩት ስድስት በሴቶች የሚመሩ አደረጃጀቶችን ሀገር በቀል ድርጅቶች መካከል የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት እና የኢትዮጵያ ሴት ጠበቆች ማህበር የሚገኙበት ሲሆን የተፈጻሚነት ጊዜም ለአምስት አመታት የሚቆይ ይሆናል፡፡
