Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከየሁሉ ብድርና ቁጠባ መሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበር ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና የፋይናንስ ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት (MoU) ከየሁሉ ብድርና ቁጠባ መሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበር ጋር ተፈራረመ።
በስነስርዓቱ ላይ የተገኙት በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችና ህጻናት ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ ክብርት ሂክማ ከይረዲን እንደገለፁት መንግስት የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል:: ሚኒስቴር መ/ቤቱም ይህንን ስራ ለማጠናከር በገጠርና በከተማ የሚገኙ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን ትኩረት በመስጠት በመስራት ላይ መሆኑን ገልፀው የዛሬው ስምምነትም አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል። ለአምስት ዓመታት ጸንቶ የሚቆየው ይህ የትብብር ስምምነት በዋናነት ለሴቶችና አነስተኛ ገቢ ላላቸው ስራ ፈጣሪዎች ተስማሚ የሆኑ የብድርና ቁጠባ አገልግሎቶችን ለማመቻቸት ያለመ ነው። ከዚህ በተጨማሪም በፋይናንስ እውቀት፣ በስራ ፈጠራ፣ በስራ አመራርና በስራ መሪነት ዙሪያ ለሴቶች ስልጠናዎችንና የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት በስምምነቱ የተካተቱ ዋና ዋና የትብብር መስኮች መሆናቸውን ገልፀዋል።
በተጨማሪም በሴቶች የሚመሩ አነስተኛ የንግድ ስራዎችን በመደገፍ የራሳቸውን ገቢ እንዲፈጥሩና በራሳቸው እንዲቆሙ ከማድረግ ባለፈ፣ ከመንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር በመተባበር ለሴቶች ልማት የሚሆኑ ሀብቶችን ማሰባሰብና የጋራ ጥናቶችን ማካሄድም በስምምነቱ ከተካተቱት አላማዎች መቀመጡን ተናግረዋል።የየሁሉ ብድርና ቁጠባ መሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበር ስራ አመራር ቦርድ ዋና ሰብሳቢ አቶ መሳፍንት ደበበ በበኩላቸው፣ የሁለቱ ተቋማት ቅንጅት ቁጠባንና ብድርን በማበረታታት የሴቶችን ኢኮኖሚዊ ተጠቃሚነት ለማጠናከር ትልቅ እርምጃ መሆኑን ጠቁመዋል።

በስምምነቱ መሰረት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተጠቃሚ ሴቶችን የመለየት፣ የማስተባበር፣ የፖሊሲና የቴክኒክ ድጋፍ የመስጠት እንዲሁም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን የመምራት ኃላፊነት ይወስዳል። በሌላ በኩል የሁሉ ብድርና ቁጠባ መሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበር ለሴቶች ግልጽና ፍትሃዊ የብድርና ቁጠባ አገልግሎት መስጠት፣ ለሴቶች ተስማሚ የፋይናንስ አማራጮችን ማቅረብና የፋይናንስ ምክር አገልግሎት የመስጠት ድርሻ ይኖረዋል። ሁለቱም ተቋማት ስምምነቱን በጋራ በመከታተልና በመገምገም የሴቶችን ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ እድገት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
