Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ሴት ልጅ ሰብአዊና መሰረታዊ መብቷንና ህልሟን የምታሳካበትን ኢትዮጵያን መገንባት የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የሁሉም የጋራ ኃላፊነት መሆኑ ተነገረ
ይህ የተገለጸው ያለዕድሜ ጋብቻንና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስወገድ የሚያስችል የሁለተኛው ዙር ብሔራዊ ፍኖተ ካርታ ዝግጅት የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ ነው፡፡

በመድረኩ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችና ህጻናት ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ ክብርት ሂክማ ከይረዲን እንደገለጹት፤ ያለዕድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛት በባህል ስም የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ የፆታ እኩልነት ተግዳሮቶችና የህፃናትን የወደፊት ዕድል የሚያጨልሙ ከባድ ሀገራዊ ፈተናዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ያለዕድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛት እንዲሁም ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ማስወገድ ምርጫ ሳይሆን ሕጋዊና ሞራላዊ ግዴታ እንዲሁም ሀገራዊ አደራ መሆኑን አስገንዝበዋል። ከ2020 እስከ 2024 ሲተገበር የቆየው የመጀመሪያው ብሔራዊ ፍኖተ ካርታ ለተቀናጀ ሀገራዊ ምላሽ አሰጣጥ መሠረት መጣሉን ያወሱት ክብርት ሂክማ ከይረዲን፣ የማህበረሰብ ግንዛቤን በማሳደግ በሴት ልጅ ግርዛትና ያለዕድሜ ጋብቻ ላይ የመቀነስ አዝማሚያ እንዲታይ ማስቻሉንም ጠቁመዋል።

አሁን የሚዘጋጀው ሁለተኛው ዙር ፍኖተ ካርታ (2026–2030) የቀደሙ ስኬቶችን ከማስቀጠል ባለፈ መሰረታዊና ቁልፍ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የአሰራር ስርዓት የሚዘረጋ፣ በማስረጃ ላይ የተመሠረተ፣ በቂ ፋይናንስ ድጋፍ ያለው እና ግልጽ የተጠያቂነት ሥርዓት የሚያስቀምጥ ሀገራዊ የተግባር ማዕቀፍ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል። ሴት ልጅ ሰብአዊና መሰረታዊ መብቷን ህልሟን የምታሳካበትን ኢትዮጵያ መገንባት የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የሁሉም የጋራ ኃላፊነት መሆኑን በአጽኖት ተናገረዋል፡፡ በመድረኩ ከተለያዩ የፌደራል ተቋማት፣ ከፍትህ ቢሮ፣ ከጤና ቢሮ ፣ትምህርት ቢሮ እንዲሁም የሴት ልጅ ግርዛትና ያለእድሜ ጋብቻ ለማስቀረት የተቋቋመው ብሄራዊ የጥምረቱ አባላት ተገኝተዋል፡፡
