ህፃናት የዛሬ ብቻ ሳይሆኑ የነገ ተስፋ መሆናቸውን በመገንዘብ መንግስት ለህፃናት ጥበቃ፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ምግብ እና ደህንነት ትኩረት በመስጠት ተጨባጭ ስራዎችን እያከናወነ ነው- ክብርት ሂክማ ከይረዲን

ይህን የተናገሩት ተቋማዊ የህፃናት እንክብካቤ አማራጮች የመጨረሻው ውሳኔ ሊሆኑ እንደሚገባ የሁሉን አቀፍ የህፃናት እንክብካቤ ማሻሻያ (MCCR) ማዕቀፍ ፕሮግራምን ለመከለስና ለማስተካከል ያለመ አህጉር አቀፍ ምክክር መድረክ ላይ ነው።

የኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደሮች ኢትዮጵያ ከኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደሮች ዓለም አቀፍ ጋር በመተባበር ባተዘጋጀው በዚህ መድረክ ላይ የሚኒስቴሩ የሴቶችና ህፃናት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክብርት ሂክማ ከይረዲን እንደገለፁት ህፃናት የዛሬ ብቻ ሳይሆኑ የነገ ተስፋ መሆናቸውን በመገንዘብ መንግስት ለህፃናት ጥበቃ፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ምግብ እና ደህንነት ትኩረት በመስጠት ተጨባጭ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ማንኛውም ህፃን በአስተማማኝ፣ በፍቅርና ክብካቤና በቤተሰብ አካባቢ የማደግ መብቱን ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸው፣ ተቋማዊ የእንክብካቤ አማራጮች የመጨረሻው ውሳኔ ሊሆኑ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በአሁኑ ወቅትም ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት የቅድመ ልጅነት እድገት ፕሮግራሞችን በማስፋፋት እያንዳንዱ ህፃን ደህንነቱ በተጠበቀ እና ቤተሰባዊ ፍቅር በተሞላበት አካባቢ የማደግ እንዲሁም አቅሙን በመጠቀም ምቹና ለህፃናት ዕድገት መሠረት የሚሆኑ ስራዎች በመሰራት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል። ምንም እንኳን ህፃናት በቤተሰብ ጥበቃና ክብካቤ ስርዐት ማደጋቸው ቅድሚያ የሚሰጠው ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር ተጋላጭ የሁኑ ልጆችን አሁን ላይ የሀገር ውስጥ ጉዲፈቻንና የህፃናት ማቆያና መንከባከቢያ ማዕከላት ውስጥ የሚገኙ ህፃናት መረጃቸው ተጠብቆና ደህንነታቸው ተረጋግጦ እንዲያድጉ የሚያስችሉ ተግባራትንም በማከናወን ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም ተቋማት ከእንክብካቤ የሚወጡ ወጣቶችን መረጃ በህፃናት ጥበቃ መረጃ አስተዳደር ስርዓት (CPIMS+) ውስጥ ለማካተት የተከናወኑ ስራዎችም የመረጃ ጥራትን ለማረጋገጥ እና የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። በተጨማሪም ከኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደሮች ጋር በመተባበር የተከናወኑ እንደ አማራጭ የህፃናት እንክብካቤ መመሪያ፣ የአዲሱ ህፃናት አዋጅ ረቂቅ እና የመረጃ ሥርዓትን ማጠናከር በጋራ ከተሠሩ ስራዎች መካከል መሆኑን ገልፀዋል።

በኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደሮች ዳይሬክተር አቶ ሳህለማሪያም አበበ በበኩላቸው፣ በአፍሪካና ኢትዮጵያ ለሚገኙ ለችግር ተጋላጭና ከቤተሰብ ክብካቤ ውጭ ለሚኖሩ ህፃናት የድጋፍ ስርዐቱን የተቀናጀ እና የተጠናከረ በማድረግ የጋራ ሥራ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል። በምክክር መድረኩ ላይ የመንግሥት ተወካዮች፣ የህፃናት መብትና ደህንነት ባለሙያዎች እንዲሁም ከቤኒን፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ማላዊ የተወጣጡ አጋር አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

Please follow and like us: