“የሳባ ንግግሮች” መድረክ – ‘የሴቶችን መሪነት እና በዲፕሎማሲ ውስጥ ትርጉም ያለው ተሳትፎ ማድረግ የሚችሉበትን ልምድ ለመለዋወጥ የጎላ አስተዋፅኦ ማበርከቱ ተገለፀ

‎የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የውጭ ጉዳይ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት (IFA) “ያለፈውን ማክበር፣ የአሁንን ማብቃትና የወደፊቱን መቅረጽ” በሚል መሪ ቃል የሩብ ዓመቱ የ”ሳባ ንግግሮች” መድረክ አካሂደዋል።
‎‎መድረኩ የትውልዶች የልምድ ልውውጥን ለማበረታታት እና ሴቶች በዲፕሎማሲ ላይ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማድረግ ያለመ ነው። በመድረኩ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ዲፕሎማቶች እና የክልልና ዓለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮች የተገኙ ሲሆን በዕለቱ የአምባሳደር ቆንጂ ሥነጊዮርጊስን ታሪክ እና አስተዋጽኦም ተዘክሯል። ‎የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ዴኤታ ክብርት ሂክማ ከይረዲን በዚሁ ጊዜ፥ ሴቶች በባለቤትነት፣ በውሳኔ ሰጪነት እና በዲፕሎማሲ ውስጥ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው ትልቅ ድጋፍና ምቹ ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቺፍ ኦፍ ስታፍ አዳም ተስፋዬ መድረኩ የትውልዶች እውቀት ሽግግርን እውን በማድረግ ረገድ ያለውን ሚና አጉልተው፥ የኢትዮጵያ የውጭ አገልግሎት እና የአፍሪካ ህብረት ተቋማዊ ትውስታን ለማጠናከር ያለውን ጠቀሜታ አያይዘው ገልጸዋል።
‎የዲፕሎማሲ ተቋማት በፍጥነት እየተለወጠ ባለው ዓለም አቀፍ ሁኔታ ውስጥ እየተጣጣሙ ጠቃሚ እሴቶችን መጠበቅ እንዳለባቸውም አፅንዖት ሰጥተዋል። በኢትዮጵያ የኢጋድ ልዩ መልክተኛ አበበው ቢሆንኝ እና የውጭ ጉዳይ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር መሀመድራፊ አባራያ አባቡልጉ በበኩላቸው፥ በዲፕሎማሲ እና የውጭ ፖሊሲ ሂደቶች ውስጥ የሴቶች ትርጉም ያለው ተሳትፎ እና ተጽዕኖ ፈጣሪነት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል። ‎በኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር ዑባ መሀመድ መድረኩ ለውይይት፣ ለግንዛቤ እና ለሀሳብ ልውውጥ ዋና መድረክ መሆኑን ገልጸው፣ “የሴቶች ዲፕሎማሲያዊ አመራርን ማጠናከር ውክልናን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ዲፕሎማሲያዊ አቅም ትልቅ ኢንቨስትመንት ነው” ብለዋል።
‎መድረኩ በማደግ ላይ ባለው የክልልና ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ሁኔታዎች ውስጥ ሴቶች በሊቀመንበርነት፣ በድርድር እና በውሳኔ ሰጪነት ያላቸውን ተሳትፎ እና ውክልና በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ የተደረጉ አቀራረቦችን እና ውይይቶችን ማስተናገዱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
‎
Please follow and like us: