እንክብካቤ ወጪ አይደለም፤ በሰው ኃይል እና በአህጉሪቱ ዘላቂ ልማት ላይ የሚደረግ ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንት ነው – ክብርት ሁሪያ አሊ

‎”የእንክብካቤ ስራዎችን በአፍሪካ የልማት አጀንዳ ማዕከል ማድረግ” በሚል መሪ ቃል በአህጉር ደረጃ የመጀመሪያው የሆነው የአፍሪካ የእንክብካቤ ፎረም (Africa Care Forum) በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
‎‎በመድረኩ መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ፥ በመላው አፍሪካ የሚከናወኑ የእንክብካቤ ስራዎች ክፍያ የሌላቸው፣ እውቅና ያላገኙ እና በዋናነት በሴቶች እና በሴት ልጆች ትከሻ ላይ የወደቁ በመሆናቸው የትምህርት፣ የስራ እድል እና የውሳኔ ሰጭነት ተሳትፏቸው ላይ ትልቅ እንቅፋት እንደሚፈጥር ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በቅርቡ ባጸደቀችው የሴቶች ማብቃትና የስርዓተ ጾታ እኩልነት ፖሊሲ እንዲሁም በሴቶች ኢኮኖሚያዊ ማብቃት ስትራቴጂ አማካኝነት ያልተከፈሉ የእንክብካቤ ስራዎችን እውቅና በመስጠትና ጫናቸውን በመቀነስ ረገድ በርካታ ስራዎችን እየሰራች ይገኛል ብለዋል።
‎‎የመንግስት ተቋማት የህፃናት ማቆያ ቦታዎችን እንዲያዘጋጁ ህጋዊ መመሪያ ተሰጥቶ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አፈጻጸሙን በቅርበት እየተከታተለ እንደሚገኝም ጠቁመዋል። ‎የእንክብካቤ ስራን እንደ ቀላል ወጪ ሳይሆን ለሰው ሀብት፣ ለእኩልነትና ለአህጉሪቱ ዘላቂ እድገት (አጀንዳ 2063) የሚያስፈልግ ትልቅ የኢንቨስትመንት ዘርፍ አድርጎ በመመልከት፤ አፍሪካውያን አህጉራዊውን የእንክብካቤ ማዕቀፍ በማጠናከር ለዘላቂ ልማት እና እድገት በጋራ እንዲቆሙ ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ ጥሪ አቅርበዋል። ኢትዮጵያ ፍትሃዊ፣ ሁሉን አቀፍ እና ምላሽ ሰጪ የእንክብካቤ ሥርዓቶችን ለመገንባት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።
Please follow and like us: