Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
በተጋላጭ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ፍልሰተኞች የሚደረግ ጥበቃና ድጋፍ ላይ ያተኮረ ሁለተኛ ዙር ስልጠና በጅማ ከተማ ተካሄደ
በሰዎች የመነገድና ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል ተጎጂዎች እና በተጋላጭ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ፍልሰተኞች የሚደረግ ጥበቃና ድጋፍ ላይ ያተኮረ ሁለተኛ ዙር የአቅም ግንባታ ስልጠና በጅማ ከተማ ተካሂዷል።
ስልጠናው የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) ጋር በመተባበር፣ ከኔዘርላንድ መንግሥት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የተዘጋጀ እንደሆነ ተመላክቷል። በሁለተኛው ዙር ስልጠና ከኦሮሚያ ክልል ማዕከላዊና ምዕራብ ዞኖች የተውጣጡ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮዎች ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

ስልጠናው በዋናነት በብሔራዊ የቅብብሎሽ ሥርዓት (National Referral Mechanism—NRM) አተገባበር ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ በሰዎች የመነገድ ወንጀል ተጎጂዎችንና በተጋላጭ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ፍልሰተኞችን በወቅቱና በተገቢው ለመለየት፣ የጥበቃ ፍላጎታቸውን ለመገምገም፣ ተገቢውን የጥበቃና የድጋፍ አገልግሎት ማግኘታቸውን ለማረጋገጥ የበኩሉን አገዛ ያደርጋል:: ስልጠናው ዘላቂ ማኅበራዊ መልሶ ማቀላቀልን ማጠናከር ላይ የተሠማሩ ሙያተኞች በዘርፉ ያላቸውን ተግባራዊ እውቀትና ክህሎት ለማዳበር ያለመ ነው።
በክልልና በዞን ደረጃ የሚገኙ ባለሙያዎች የተጎጂዎችን መብት፣ ክብርና ደህንነት በማስጠበቅ፣ የተቀናጀ፣ ተደራሽና ተጎጂ ተኮር የጥበቃና የድጋፍ ሥርዓትን በተግባር እንዲያስፈጽሙ አቅማቸውን የማጠናከር ሥራ በቀጣይነት እንደሚከናወን ተጠቁሟል።
Please follow and like us:
